ከመሞት…መሰንበት!

569

በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

የሰው ልጆችን ለሞት ይዳርጋሉ ተብለው በአሳሳቢነታቸው ከአንድ እስከ አስር ከተዘረዘሩት መካከል በገዳይነቱ በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይመደባል። ለብዙዎቹም እልቂትና ንብረት መውደም ምክንያት ነው፡፡ ለአፍታም ቢሆን ቆም ተብሎ ቢታሰብ በዚህ አደጋ ከትምህርት ገበታ የተለዩ ሕፃናትና ታዳጊዎችን ጨምሮ አባትና እናት ማለዳ ከቤት በሰላም ወጥተው  ሳይመለሱ ከማስቀረቱም በላይ አገር ሰላም ብለው በተኙበት አስቀርቷል። ይህ አሰቃቂውና በአብዛኛው በጥንቃቄ ጉድለት የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ ነው። የአለም የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2018 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያስረዳው በአመት ከ1 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በአደጋው ይሞታሉ።

የድርጅቱ መረጃ እንደሚያሳየው በአመት በትራፊክ አደጋ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ ሰዎች መካከል በአፍሪካ የአደጋው መጠን 26 ነጥብ 6 በመቶ ሲሆን በአውሮፓ ደግሞ 9 ነጥብ 3 በመቶ ነው። በዚህ አሰቃቂ አደጋ ከ15 እስከ 44 ዕድሜ የሚገኙ ሰዎች የሚቀጠፉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ደግሞ 77 በመቶዎቹ ወንዶች እንደሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ። በትራፊክ አደጋ ጉዳት የሚደርስበትን የዕድሜ እርከን ስንመለከት ደግሞ አህጉሪቱ ወጣትና አምራች ሃይሏን እያጣች እንደሆነም የሚጠቁም ነው።

በአለም ላይ በቀን ከ3 ሺ 7 መቶ በላይ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ የአካል ጉዳተኛ እንደሚሆኑና ከዚህም መካከል ህጻናት፣ እግረኞች፣ ሳይክል ተጠቃሚዎችና፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎች በመጀመሪያው ረድፍ ተጎጂ እንደሚሆኑ የአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል። ይህን አሰቃቂ አደጋ ለመቀነስ ድርጅቱ ከወላጆች፣ ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየሰራ እንደሆነ ጠቁሟል። የችግሩን አሳሳቢነት በማስረዳት የአመከለካከት ለውጥ በማምጣት የፍጥነት ገደብ ማስቀመጥ፤ ጠጥቶ አለማሽከርከር፣ የፍጥነት መቀነሻ መንገድ መዘርጋት፣ የሞተሮችን ሄልሜት መጠቀም እና የደህንንት ቀበቶ መጠቀም በሚቻልበት ዙሪያ እየሰራ እንደሆነ በሪፖርቱ አካቷል።

በተሽከርካሪ ቁጥር ከአፍሪካ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘዋ አገራችን በትራፊክ አደጋው ግን በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሆነች የየቀኑ የአደጋ ሪፖርቶች ማረጋገጫዎች ናቸው።  በአለማችን የተመዘገበ ከ6ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች ያሏት አውሮፓዊቷ አገር  ኖርዌይ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት በትራፊክ አደጋ ያጣቸው አንድ ሰው ብቻ ነው። የአደጋው ውጤት ዝቅትኛ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የቁጥጥርና የአሰራር ስርዓቷ ጥብቅ መሆኑ፤ ዜጎቿ የትራፊክ ህግን አክብረው ለማስከበር ያላቸው ቀናኢነት፣ እንዲሁም የመንገዶቿ ዘመናዊነት እና የዘርፉ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወዘተ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

በአንፃሩም ሃገራችን በአነስተኛ የመኪና ቁጥር በየጊዜው በሚያጋጥሙ የትራፊክ አደጋዎች በርካቶች የጉዳት ሰለባ ሲሆኑ ማስተዋል ይቻላል። የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባወጣው ሪፖርት መሰረት በ2011 ዓ.ም. ብቻ በመንገድ ትራፊክ አደጋዎች ሳቢያ 4 ሺህ 597 ሞት፣  7 ሺህ 047 ከባድና 5 ሺህ 949 ቀላል የአካል ጉዳቶች ሲመዘገቡ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረትም ወድሟል፡፡ ይህም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር፣ ሞት በ52 ነጥብ 1 ወይም 10 ነጥብ 07 በመቶ፣ ከባድ የአካል ጉዳት በ347 ወይም 4 ነጥብ 47 በመቶ እንዲሁም ቀላል ጉዳት በ1 ሺህ 826 ወይም 23 ነጥብ 48 በመቶ መቀነስ ቢያሳይም አደጋው እስካሁን እንደቀጠለ ነው።

ለትራፊክ አደጋው እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የመቀመጫ ቀበቶ አለመጠቀም ብሎም አለማጥበቅ፣ የሕፃናት ድጋፍ አለመጠቀም፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ችግር፣ የተሽከርካሪዎች ቴክኒካዊ ችግር፣ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት አለመስራት እንዲሁም የተሳፋሪዎች እና እግረኞች ጥንቃቄ ጉድለት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ጠጥቶ ማሽከርከር የሚለው በየጊዜው የሚከሰተው ጥፋት ከስነ ምግባር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ቢሆንም ለጥፋቱ መከሰት በዋናነት  የሚጠቀሰው የቁጥጥር መላላት እንደሆነ ብዙዎቹ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። በቁጥጥር ሂደት ሲገኝም የሚቀጣው ቅጣትና ያጠፋው ጥፋት ተመጣጣኝ አይደለም የሚሉትም በርካቶች ናቸው። የትራፊክ መቅጫ ህግ እንደሚለው ለመጀመሪያ ጊዜ ህጉን ተላልፎ የተገኘ 300 ብር ቅጣትና ለጥፋቱ አራት ነጥብ ተመዝግቦበት፣ የተመዘገበው የጥፋት ነጥብ 17 ሲያልፍ እንደ ተመዘገበበት ነጥብ ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት የአሽከርካሪ ብቃት ዕገዳ ይጣልበታል። ይህ እንግዲህ አይደለም ለማገድ የመጀመሪያው የጥፋት ቅጣት ከሰው ልጅ ህይወት አንጻር ሲታይ አስቂኝ ከመሆኑም በላይ በርካታ ስራዎችን በመስራት በትንሹ ከፍሎ ማለፍን እንዲመርጥ የሚያደርግ አበረታች ቅጣት ነው ሲሉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

ከመጀመሪያው የመውጫ ወረቀት ሲያወጣ መጠጣት አለመጠጣቱን የማረጋገጫ መንገዶችን መከተል አስቀድሞ አደጋን ለመከታተል ያግዛል።    መሰል የህገ ወጥነት አይነቶች ደግሞ በክልሎች አገር አቋራጭ  የሚሰሩ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶች እንደሁም በተለምዶ አባዱላ ተብለው በሚጠሩት ተሽከርካሪዎች ላይ ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም ጉዳቱ በጭነት መኪኖችም የሚበረታ እንደሆነ የትራፊክ ፖሊስ የሰርክ ሪፖርት ያሳያል። ሌላው ከአልኮል መጠጥ ባልተናነሰ አሁን አሁን እንደ ምክንያት የሚወሰደው ጫት እየቃሙ እና ቅሞ ማሽከርከርም አንዱ ነው። እዚህ ላይ መረዳት ያለብን ጫት ቅሞ ማሽከርከር የሚያመጣውን ጣጣ እምብዛም መገናኛ ብዙሃኑ ተጨንቀው ትምህርት  ሲሰጡበት አለመታየቱ ነው። በጫት ለመረቀነ አሽከርካሪ የሚታየው ደግሞ ገደሉ ሜዳ ሆኖ ነውና ከጥንቃቄ እንዲዘናጋ በማድረግ አስከፊና ዘግናኝ አደጋን እንዲያደርስ ያደርገዋል። በበርካታ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ላይ ለሚያጋጥሙ አደጋዎች በአብዛኛው ረጅም ጉዞን ያለ እረፍት ማሽከርከር፤ ከድካሙም ለመውጣት ጫትን የመሰሉ አደንዛዝ እፆች መጠቀም እንደሆነም ይነሳል።

በሁለተኛ ደረጃ እንደምክንያት የሚወሰደው ደግሞ የአሽከርካሪ ብቃት ብሎም የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት ነው። የመንጃ ፈቃድ ለማግኘት የዕድሜውና የአዕምሮው ብሎም ሙሉ የአካላዊ ጤንነቱን ባገናዘበ መልኩ መሆን እንዳለበት የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥና ደምብ ያስረዳል። አሁን አሁን  ግን ጎልቶ እየታየ ያለው በመጀመሪያ ዕድሜው 18 አመትና ከዚያ በላይ የትምህርት ዝግጅቱ ደግሞ ስምንተኛ ክፍልን ያጠናቀቀ እንዲሁም ሙሉ አካላዊ ጤንነቱ የተረጋገጠ ብቻ ነው ቢልም ዕድሜውን ከፍ በማድረግ የትምህርት ዝግጅቱን ደግሞ በሃሰተኛ መልክ በማውጣት መንጃ ፈቃድ እንዲያገኝ ይደረጋል።

በተለይ የሜዲካል ነገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ በአራዳ ጤና ጣቢያ ነርስ የሆነችው ሲስተር ዘይነባ መሀመድ ትናገራለች። ባለሙያዋ እንደምትለው ማንኛውም ሰው የማውጫውን ገንዘብ እስከከፈለ ድረስ እንደሚሰጠውና በአሰጣጡም ጊዜ ጠለቅ ያለ ምርመራ እንደማይደረግም አስረድታለች። “ስለሆነም የቁጥጥሩና ክትትሉ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የሚጠቁም ጊዜ ላይ እንዳለን ማሳያ ነው።” ብላለች። የሚመለከታቸው አካለት ከመንገድ ትርንስፖርት፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት እንዲሁም ከአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር ተናበው መስራት እንደሚገባም ባለሙያዎች ያሳስባሉ።

በተመሳሳይ ደረጃ ለአደጋው መበራከት እንደምክንያት የሚወሰደው ደግሞ አሽከርካሪዎች በተለይም ክፍለ ሀገር የሚሰሩ ከተፈቀደለት የፍጥነት መጠን በላይ መንዳት እንደሆነ በተለያዩ ጊዚያት የሚወጡ የትራፊክ አደጋ ሪፖርቶች ያስረዳሉ። ለዚህ ማሳያው በታህሳስ 30/2012 ዓ.ም በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ በትራፊክ አደጋ የ4 ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት ሲሆን የአደጋው መንስኤ ከተፈቀደው የወንበር ቁጥር በላይ መጫን እና ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር መሆኑን ስንሰማ በራስ ሁኔታ እራስን ማጥፋት አይነት ዕኩይ ተግባር እንደሆነ ማሳያ ነው። ይህ ደግሞ በዋናነት አሁን አሁን በደረጃቸውና በይዘታቸው ላቅ ብለው የተገነቡት መንገዶች ላይ በብዛት ይስተዋላል።

ለዚህም መንገዶች ደረጃቸውን የጠበቁ ካለመሆናቸው በተጨማሪ የተሽከርካሪውን የቴክኒክና የአቅም ደረጃ ሳይፈትሹ ብሎም ቶሎ ቶሎ የመስራት ፍላጎት ተጨምሮ አደጋውን የከፋ ያደርገዋል። ይህንን ለመፍታት በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች የሚገኙና ከ2000 ኪሎ ሜትር በላይ ሆነው አደጋ የሚከሰትባቸው መንገዶች ተለይተው የኢንጂነሪንግ ማሻሻያ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እንደተከናወነና የመንገድ ትራፊክ ሥራን በጥራትና በቅልጥፍና የሚመራ ተቋም ለማቋቋም የሚያስችል እንቅስቃሴ እንደተጀመረ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ተናግረዋል።

በተለይ ህዝብ ማመላለሻ በፍጥነት ያሰቡበት ቦታ በመድረስ ብዙ ጊዜ መመላለስን መሰረት ያደረገ እንደሆነ የሚታይ እውነታ ነው። ለዚህ ደግሞ ችግር ዋነኛው ምክንያት በየቦታው የሚገኙ የትራፊክ ማኔጅመንት አባላት እነዚህ ቶሎቶሎ የሚመላለሱ መኪኖችን መቆጣጠር ቢቻል የሚል ሀሳብ ከህዝቡ ይንጸባረቃል። ይህን ከልክ ያለፈ ፍጥነትን ለመቀነስ ከታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሦስተኛው አገራዊ የመንገድ ደህንነትና የትራንስፖርቴሽን አገልግሎት ቁጥጥር መጀመሩን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስረድቷል። በዚህም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ቁጥጥር እየተተገበረ እንደሆነ  በባለስልጣኑ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ በላይ ተናግረዋል። ቁጥጥሩም  የደህንነት ቀበቶ መታጠቅ፣ የአልኮል ፍተሻ፣ የፍጥነት ወሰን መገደቢያና ራዳር ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሚሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

አደጋውን ለመቀነስ በመንግስት በኩል ከሚታዩ የህግ ማስከበር ክፍተቶች ባሻገር እያንዳንዱ የመንገድ ተጠቃሚ ያለው ቸልተኝነት ዋነኛው ነው፡፡ በተለይ ለአደጋ መከሰት ትልቅ ድርሻ ያላቸው አሽከርካሪዎች ለጥንቃቄ የወጡ ህጎችን አለማክበር የትራፊክ አደጋን አባብሶታል፡፡ አሽከርካሪን የሚደግፉ አስከባሪም ሆነ መንገደኛም እንዲሁ ለህግ መከበር የሚሰሩት እና የሚያከብሩት እንደተጠበቀ ሆኖ የዓለም ጤና ድርጅት በሕዝብ ትራንስፖርት አማካኝነት የሚንቀሳቀሱ አካላት በጉዞ ወቅት የደህንነት ቀበቶ በአግባቡ ቢጠቀሙ፣ አደጋ በሚያጋጥማቸው ወቅት አሽከርካሪውንና ከፊት የሚቀመጡ ሰዎች ከ40 ከመቶ እስከ 50 በመቶ ለሞት ተጋላጭነታቸውን እንደሚቀንስ ያስቀምጣል።  በመሆኑም የመንገድ ትራፊክን ለመቆጣጠር የወጣ የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 208/2003፣ ማንኛውም አሽከርካሪ ከባጃጅ ሞተር እና በግዳጅ ላይ ከተሰማሩ ተሽከርካሪዎች ውጪ ሁሉም ተሽከርካሪዎች የደህንንት ቀበቶ ሳያስር ማሽከርከር እንደሌለበት እና በተሽከርካሪ ውስጥ የተሳፈረው ሰው የደህንነት ቀበቶ ማሰሩን ማረጋገጥ እንዳለበት የሚደነግገው ህግ ከጥር 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል።

በየጊዜው አደጋ የሚያደርሱ አሽከርካሪዎች እንዳሉ ሁሉ ለበርካታ አመታት ምንም አይነት አደጋ ያላደረሱ ምስጉን አሸከርካሪዎች እንዳሉ መዘንጋት አያስፈልግም። በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነው የአውቶቡሶችና የታክሲዎች የጉዞ ዕቅድ መተግበሪያ ዲጂታል ካርታ፣ ይፋ በሆነበት ወቅት እንደተገለጸው ከአምስት እስከ አሥር ዓመታት ድረስ በራሳቸውም ሆነ በሌላው ላይ አደጋ ያላደረሱ፣ አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የሕዝብና የጭነት ማጓጓዣዎችን ያሽከረክሩ የነበሩ 120 ጠንቃቃ ሾፌሮች  በቅርቡ ተሸላሚ ነበሩ። ከተሸላሚ ሾፌሮችም መካከል፣ 50 ሾፌሮች ለሽልማት የሚያበቃቸውን ስምንት የተለያዩ መስፈርቶችን ከ90 እስከ 100 በመቶ በማምጣት በከፍተኛ ደረጃ ያለፉ ምርጦች መሆናቸው በመድረኩ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ለአደጋው መበራከት እንደምክንያት እየሆነ የመጣው አሳሳቢ ነገር አገራችን ውስጥ ከሚገኙት 1ሚሊዮን የሚጠጉ መኪኖች መካከል አብዛኛዎቹ ያገለገሉና በርካሽ ዋጋ ወደ አገር ውስጥ የገቡ እንደሆኑ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ይጠቁማል። ይህን አይነት ችግር ይቀርፋል ተብሎ ከታሰበ አሰራር መካከል የኤክሳይዝ ታክስ ተግባራዊ መሆን ችግሩን በዘላቂነት ይፈተዋል ባይባልም የራሱን በጎ ሚና ግን ይጫወታል።

በመሆኑም ይህንን አሰቃቂ እና የዕለት ተዕለት ገዳይ አደጋ  ከሥር መሠረቱ ለመቆጣጠር፣ የዕጩ አሽከርካሪዎች የሥልጠና አሰጣጥን ለማሻሻልና የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በሚገባ ከማረም ጀምሮ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ እንዲሁም ከመንገድ ትራፊክ አደጋ የተጠበቀ ማኅበረሰብ በመፍጠር ሰላማዊ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር የሚደረገው ጥረት አደጋውን ከመቀነስ አኳያ ድርሻው ላቅ ያለ ነውና ሁሉም ዜጋ በትብብር ሊሰራ ይገባል መልዕክታችን ነው።