በመጪዎቹ አስር አመታት በመላው አገሪቱ ከ 4 ሚሊዮን በላይ ቤቶች ለመገንባት ታቅዷል

152
ጥር 9 / 2012 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ በመጪዎቹ አስር አመታት በተለያዪ ከተሞች 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፍ በመጪዎቹ አስር አመታት እቅድ ላይ ሲያካሂድ የነበረው የሁለት ቀን የግብአት ማሰባሰቢያ ውይይት በዛሬው እለት ተጠናቋል። እቅዱ ከቀጣይ 2013 ዓ.ም ጀምሮ የሚተገበር ሲሆን እቅዱን እውን ለማድረግ" የተቋማት ተግባቦት፣ ቅንጅትና ቁርጠኝነት "ሊታከልበት እንደሚገባ የከተማ ልማትና ኮንስትራከሽን ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ ተናግረዋል። መሪ እቅዱ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆን ዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት ከፌደራል እስከ ክልል ከተሞች ድረስ በተዋረድ የሚተገብሩት መሆኑም ተገልጿል። በእቅዱ ላይ የስራ አጥነት፣ የመሰረተ ልማትና የመኖሪያ ቤት እጥረት የሀገሪቱ ዋነኛ ተግዳሮቶች መሆናቸውንና በምን መንገድ እንደሚፊቱም ተመላክቷል። ከዚህ ውስጥ በከተሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል በቀጣይ አስር አመት 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት በእቅዱ ላይ ተቀምጧል። ባለፉት 13 አመታት የተገነቡት መኖሪያ ቤቶች ከ400 ሺ አለመብለጣቸውን በማስታወስ  በቀጣይ አስር አመት 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን መኖሪያ ቤት እንዴት መገንባት ይቻላል የሚል ጥያቄ በውይይቱ ላይ ተነስቶም ነበር። በዋናነት መንግስት በግንባታው ላይ የግል ባለሃብቶች የግብአት እቃ  አቅርበው እንዲሰሩ የጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በአጭር ጊዜ ቤቶችን ለመስራት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበትን ሁኔታ ያመቻቻል ሲሉ ሚኒስትሯ ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት የቤት ግንባታ ግብአትን በሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ማምረት መጀመሩ የተገለፀ ሲሆን ይህም የተገጣጣሚ ቤት አሰራር ቴክኖሎጂ እቅዱን ለማሳካት አጋዥ እንደሚሆን አክለዋል። ለቤቶቹ ግንባታ የሚያስፈልገው 80 በመቶ ግብአት ከሀገር ውስጥ ለመጠቀም መታሰቡም ተገልጿል። በኮንስትራክሽን ዘርፍ በተሰማሩ  የግልና የመንግስት አካላት እና ተቋማት ዘንድ የሚታየውን ብልሹ አሰራር ማስተካከል ከተቻለ እቅዱ እንደሚሳካ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ ተናግረዋል። በኮንስትራክሽን ዘርፉ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆነው በቀጥታ በዘርፉ ስራ የሚፈጠርለት ሲሆን ቀሪው በተዘዋዋሪ የስራ እድል ባለቤይ ይደረጋል ተብሏል። በአጠቃላይ የስራ አጥነትን፣ የመሰረተ ልማትና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት አንዲሁም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተያዘውን  እቅድ ለማሳካት የሁሉም ተቋማትና ዜጋ ጥረት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም