የአይደር ስፔኛላይዝድ ሆስፒታል ለ12 ሰዎች ነፃ የማይክሮ ቫስኩላር ህክምና መስጠቱን ገለፀ

58
መቐለ ኢዜአ 9/5/12 የአይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከቼክ ሪፐብሊክ የህክምና ቡድኖች ጋር በመተባበር በአደጋና በተለያዩ ህመሞች ምክንያት የፊት ላይ ከፍተኛ የአጥንት ስብራትና ጉዳት ለደረሰባቸው 12 ሰዎች በሃገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የማይክሮ ቫስኩላር ህክምና በነፃ መስጠቱን ገለፀ ። የህክምናውን ዓይነት ከተጎጂው ወገን ጤነኛ አካል አጥንት የደም ቧንቧና ስጋ በመውሰድ በተጎዳው አካል ላይ ተከላ ማካሄድ መሆኑን ተገልፇል። ህክምናው የተደረገው መቐለ ዩኒቨርሲቲ የዓይደር  ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከቼክ ሪፐብሊክ የህክምና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ነው። በዓይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአፍ መንጋጋና ፊት ቀዶ ጥገና ሰፔሻሊሰት ዶክተር መለስ ታቦር እንደገለጹት በአደጋና በተለያዩ ህመሞች ምክንያት የላይኛውና የታችኛው መንጋጋ ስብራት የነበራቸው 12 ወገኖች  ላለፉት 15 ቀናት እስከ ትናንት እኩለ ሌሊት ድረስ ነጻ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ። ታካሚዎቹ ከሌላ አካላቸው አጥንት ተወስዶ በማይክሮ ቫስኩላር  ህክምና በመተካት ቀድሞ ወደ ነበረበት ቦታ እንዲመለስ መደረጉንም አብራርተዋል ። ማይክሮ ቫስኩላር ሰርጀሪ የተባለ ህክምና  ከቼክ ሪፐብሊክ የቀዶ ጥገና ህክም ሰፔሻሊስቶች ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳካ ሁኔታ መፈጸሙን ዶክተር መለስ ተናግረዋል። ከህሙማን ሌላኛው አካል የደም ቧንባና ስጋ በመውሰድ ከ12 እስከ 16 ሰዓታት የፈጀ ቀዶ ህክምና ተደርጎላቸው ተጎድቶ የነበረውን አካላቸው ወደ ቀድሞ ይዞታው እንዲመለስ  ተደርጓል ነው ያሉት ። ህክምናው በአገራቸን የማይሰጥ በመሆኑ አንድ ጉዳተኛ ህክምናውነ ለማግኘት  ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል ። አጋፔ ኢትዮጵያ የተባለ በጎ አድራጊ ድርጅት መስራችና ባለቤት ወይዘሮ ህይወት ሓዱሽ ከቼክ ሪፐሊክ የህክምና ባለሞያዎች በማስመጣት ትልቅ ውለታ እንደፈጸሙ ዶክተር መለሰ ተናግረዋል ። ከታካሚዎቹ  ባሻገር  በዓይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚገኙ ባለሞያዎች ከዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች ጋር እንዲተዋወቁና የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሸግግር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ። ቀጣይ በሆስፒታሉ  የማይኮ ሰኩላር ህክምና  ለመጀመር መነሻ እንደሚሆናቸውም ገልጸዋል። ከአማራ ክልል ደብረታቦር ከተማ የመጡ አቶ አየነው በላይነህ በሰጡት አስተያየት ልጃቸው በደረሰበት የመኪና አደጋ የራስ ቅሉና መነጋጋው ተጨፈልቆ  መልኩ እንዳልነበረ  ሆኖ እንደነበር ገልፀዋል ። በዓይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል  12 ሰዓት የጨረሰ የቀዶ ጥገና አጥንት ተከላ ህክምና ተደርጎለት አሁን የቀድሞ ቅርጹና መልኩ በመመለሱ ልጄ ዳግም እንደተፈጠረ  አየዋለሁ ብለዋል። በትግራይ ደቡባዊ ዞን ከአፍላ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ህይወት መሓሪ በበኩላቸው ባለቤታቸው ገደል ላይ ተንሸራትተው በመውደቃቸው ምክንያት የፊት መንጋጋቸው ተሰብሮ በህክምና ላይ ሲረዱ መቆየታቸውን አስረድተዋል። አጋጣሚ ሆኖ  ከውጭ በመጡ ባለሞያዎች  ከዐይደር ሆስፒታል ሀኪሞች ጋር በመተባበር በተደረገላቸው የአጥንት ተከላ ህክምና የተሰበረው መንጋጋቸው ተጠግኖ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም