ዩኒቨርሲቲው በህዋ ሳይንስ ረገድ የሚደነቅ ተግባር እያከናወነ ነው :- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

4482

አዳማ ጥር  09/2012… የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ በህዋ ሳይንስና አዳዲስ የመማሪያ ሶፍትዌሮችን በማበልፀግ ረገድ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የሰው ሀብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት  የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከልን ዛሬ ጎብኝተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንድገለጹት የአዳማ ሳይንስናቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ  በህዋ ሳይንስና አዳዲስ የመማሪያ ሶፍትዌሮችን በማበልፀግ ረገድ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ያደራጀው የልህቀት ማእከል ሀገሪቷ ለጀመረችው የሳይንስ፣ ኢንጅነሪግ ፣የምርምርና ጥናት ሥራዎች በተግባር የተደገፉ ለማድረግ የአይስቲና የህዋ ሳይንስ ፕሮግራሞች ትልቅ ልምድ የሚቀሰምበት መሆኑን ገልጠዋል።

ተማሪዎች በኤሌክትሮንክ ትምህርት የሚማሩበትና ተሞክሮ የሚለዋወጡበት ሶፍትዌር በማበልፀግ ፣የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከሀገሪቷ የልማትና የማደግ  ፍላጎት ጋር በማገናኝት እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን አምባሳደር መስፍን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው መንግስት የመደበለትን ሀብት በአግባቡና ለታለመለት ዓላማ በማዋል

ሀገሪቷ በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስክ ያስቀመጠችውን አቅጣጫና ፖሊሲ በመከተል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የምድር ሳተላይት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ከመገንባት ጀምሮ በራሱ ተማሪዎችና መምህራን የሳተላይት ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በሀገር ደረጃ በቅርቡ ወደ ተግባር የገባውን የህዋ ሳይንስ ልማት በቀዳሚነት የሚያግዝ መሆኑንም አመልክተዋል።

አብዛኛው የመማር ማስተማር ሥራዎች በተለይም የሂሳብ፣ፊዝክስ፣እንጅነሪንግና ቴክኖሎጂ የትምህርት ፕሮግራሞች በሶፍትዌር እንዲሰጥ የኤሌክትሮኒክ ትምህርት ሥርጭት ተግባራዊ ማድረጉ ለሌሎች የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ያደራጃቸው የልህቀት ማእከላት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚፈቱ ከመሆኑም ባለፈ ሀገሪቷ ያለባትን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ክፍተት የሚሞላ ነው ያሉት ደግሞ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ዴኤታና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ናቸው።

በተለይም በትምህርት መሰረተ ልማት ግንባታ፣በጥናትና ምርምር ሥራዎች እያከናወነ ያለው ተግባር የሀገሪቷን የልማት አቅጣጫና ፍላጎት የተከተለ መሆኑን ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገልጠዋል።

የህዋ ሳይንስ፣የኬሚካል ኢንዱስትሪ ልማት፣የማማከር አገልግሎት፣በልማት ፕሮጄክቶች ዲዛይንና ጥናት፣በማህበረሰብ አቀፍ ልማት ዙሪያ ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ ያለው ሥራ ሌሎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ለተሰማሩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።

ተቋማቱ ከአዳማ ሳይንስናቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮ በመውሰድ ከመንግስት የተመደበላቸውን የህዝብ ሀብት ለታለመለት ዓላማ ማዋል አለባቸው ያሉት ፕሮፌሰሩ የህዝብ ተወካዮች ምክርት ቤት ካደረጉት ምልከታ በመነሳት  ድጋፍና ክትትል በማድረግ  ሊያግዙን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ሀገሪቷ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለባትን ችግር ከመፍታት ባለፈ በርካታ ሳይንቲስቶችን በሂሳብ፣ፊዝክስ፣ኢንጅነርንግና በሌሎች መስኮች ለማፍራት አልሞ እየሰራ መሆኑን ገልጠዋል።

ዩኒቨርሲቲው የያዘውን ግብ ለማሳካት በተለይም የለውጥ፣የመልካም አስተዳደርና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የቋሚ ኮሚቴ አመራሮች ዘላቂነት ያለው ድጋፍና ክትትል ሊያደርጉልን ይገባል ብለዋል።

የሀገሪቷን ህዝቦች ከዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያላቅቁ የልህቀት ማዕከላት በማደራጀት ጥልቀት ያላቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር ሥራዎች እያከናወነ ነው ያሉት ዶክተር ለሚ የህዋ ሳይንስ፣የኤሌክትሮንክ መማሪያ ሶፍትዌሮችና የኬሚካል ኢንዱስትሪ ልማት ፕሮግራሞች ቀዳሚ ናቸው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደቱን እንዲሳካ የአካባቢው ህብረተሰብ ፣የፀጥታ አካላትና ማህበረሰቡ ላሳየው ቁርጠኝነትና ትብብር ዶክተር ለሚ ምስጋና አቅርበዋል ።