የፋሲለደስ ትምህርት ቤት በቀድሞ ተማሪዎቹ ድጋፍ የማስፋፊያ ግንባታ ሊያካሔድ ነው

52
ጥር 9/2012  በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የፋሲለደስ ከፍተኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍል ጥበት ለመቅረፍ በውጭ አገር በሚኖሩ  የትምህርት ቤቱ የቀድሞ  ተማሪዎች ድጋፍ በ68 ሚሊዮን ብር ወጭ የማስፋፊያ ግንባታ ለማከናወን የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ። የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሽበሺ ካሰኝ በመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለፁት ትምህርት ቤቱ በርካታ ብቁ ዜጎችን ያፈራ ቢሆንም በእድሳት ማጣት ምክንያት ለጉዳት ተጋልጧል። ይህን በመረዳትም በውጭ ሃገራት የሚኖሩ አካላትን በማስተባበር ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅሰው ለማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ 20 ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል። የመጀረመሪያ ምዕራፉ ግንባታው በ3 አመታት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን 24 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለ አራት ወለል ፎቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ቀሪው የፕሮጀክቱ አካልም ደረጃ በደረጃ እንደሚከናወን ገልፀዋል ። 250 በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችከ130 ሺህ ዶላር በላይ ማዋጣታቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ሁሉንም የአካባቢው ተወላጆች በማስተባበር የትምህርት ቤቱን አደጋ ለመቅረፍ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ከተያዘው በጀት ውስጥም 54 ሚሊዮን ለመማሪያ ክፍሎች ግንባታ የሚውል ሲሆን ቀሪው 14ሚሊዮን ብር ደግሞ ለቤተ መፅሐፍት ግንባታ የሚውል መሆኑን አመላክተዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም በበኩላቸው የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎችና የአካባቢው ተወላጆች ለትምህርት ቤቱ ያደረጉት አስተዋፅኦ እንደ ሞዴል የሚወሰድ ነው፡፡ ለውጥ መፈለግና ለለውጥ መነሳት ይለያያሉያሉት ከንቲባው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን በመወጣት ለውጥን ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ያለበትን ችግር ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ ከተለያዩ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ጠቅሰው የደርባን ሲሚንቶ ፋብሪካ 5 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ ለመስጠት ቃል መግባቱን ገልፀዋል፡፡ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባሻገር የጎንደር ከተማ ባለሃብቶች በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለመለገስ ቃል መግባታቸውን ከከንቲባው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል ። ፋሲለደስ ትምህርት ቤት ከተመሰረተ 78 አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ምንም አይነት ጥገና ተደርጎላት አያውቅም ተብሏል ። በመጀመሪያ ምዕራፍ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ ስርዓት ላይ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች፣ የከተማ አስተዳሩ አመራሮችና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ አባላትና የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም