በዜማ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የተሰየመ አደባባይ ተመረቀ

189

አዲስ አበበ   (ኢዜአ) ጥር 9 / 2012  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ዜማው የላቀ ቦታ የሚሰጠው ቅዱስ ያሬድ ስም የተሰየመው አደባባይ የሃይማኖት አባቶችና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመረቀ። የቅዱስ ያሬድ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የታነፀውና ዛሬ የተመረቀው አደባባይ የሚገኘው በአዲስ አበበ ከተማ ልዩ ስሙ መስቀል ፍላውር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

አደባባዩ የተገነባው በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተክርስትያን ደብር አስተዳዳሪዎች አስተባባሪነት በ 3 ነጥብ 2 ሚሊዬን ብር ወጪ ነው።

ከዛሬ 1500 ዓመታት በፊት አክሱም እንደተወለደ የሚነገርለት ቅዱስ ያሬድ፣ በኪነጥበቡ ዘርፍ የዜማ ፈጣሪ፣ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ባለቅኔ እና ገጣሚ፣ በመንፈሳዊው ረገድ ደግሞ ጻዲቅና መናኝ  እንደሆነ ይነገራል።

ዜማዎቹም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በልዩ ሁኔታ ተቀባይነት ያላቸው ሲሆን እስካሁንም ለቤተክርስትያኒቱ  አገልግሎት እየዋሉ ይገኛሉ።

የቅዱስ ያሬድ ካዘጋጃቸው የዜማ መጻሕፍት መካከል ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬና መዋሥዕት የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በስሙ የተሰየመው አደባባይ ምርቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትሪያርክ ልዩ ጽህፈት ቤት የውጪ ግንኙነትት ኃላፊ ዶክትር ብጹዕ አቡነ አረጋዊ ባስተላለፉት መልዕከት ''ቅዱስ ያሬድ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃብት ነው'' ብለዋል።

ለቅዱስ ያሬድ የዚህ ዓይነት ቋሚ መታሰቢያ መታነፁም ሁሉንም ደስ የሚያሰኝ የተቀደሰ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

የቅዱስ ያሬድ ስራ  ከአገሪቱ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገቢውን እውቅና ያገኝ ዘንድ ቤተክርስትያኒቱ  በስፋት ትሰራለችም ብለዋል።

በዚህም መሰረት የቅዱስ ያሬድ የዜማ ሥራዎች በተባበሩት መንግስታት፣ የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተር ጥረት ይደረጋል ሲሉም  ዶክትር ብጹዕ አቡነ አረጋዊ ገልፀዋል።

ይህ እውን ይሆን ዘንድ ግን ሁሉም የሚመለከተው አካል የበኩሉን ድጋፍና ትብብር ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

የምዕራብ ሸዋ፣ የምስራቅና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት ኃላፊ ብጽዕ አቡነ ናትናኤል በበኩላቸው

''ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ባለውለታ ካህን ነው፤ ለእሱ ውዳሴ የተዘጋጀው አደባባይ ሲያንሰው ነው እንጂ አይበዛበትም'' ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ የኪነ ጥበብና የቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰርጸ ፍሬስብሃትም እንዲሁ መስሪያ ቤታቸው መንፍሳዊ ሃብቶችን የመንከባከብ ስራ በስፋት ይሰራል ብለዋል።

አቶ ሰርፀ እንዳሉት እስካሁን አስታዋሽ ያጡ መሰል ኃብቶች እውቅና እንዲያገኙና ሕዝቡም እንዲያውቃቸው በትጋት ይሰራል።

ለቅዱስ ያሬድ መታሰቢያነት ይውል ዘንድም የዜማና የቅኔ የምርምርና የስልጠና ማዕከል እንዲቃቋምም ተጠይቋል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚተዳደረውና ከ50 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረው የሙዚቃ ትምህርት ቤት "ቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት" በሚል በቅዱስ ያሬድ ስም  ተሰይሞ በስራ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም