የወጣት ዮሴፍ አያሌው የቀብር ስነስርዓት ተፈፀመ

54
ሶዶ ሰኔ 18/2010 ''ለውጥን እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበረታታ'' በሚል መሪ ቃል ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በተከሰተ የቦምብ ፍንዳታ ህይወቱ ያለፈው የወጣት ዮሴፍ አያሌው የቀብር ስነስርዓት ዛሬ በወላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ ኪንዶኮዮ ቀበሌ ተፈፀመ። ጠቅላይ  ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስልክ በመደወል ወላጅ አናቱንና ቤተሰቡን አጽናንተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ''ለአንድነት፣ ለፍቅርና ለሰላም ሲል ህይወቱን ያጣው ወጣት ዮሴፍ አያሌው  ጀግና በመሆኑ ታሪክ ያስታውሰዋል'' ብለዋል። በወላይታ ዞን የዳሞት ወይዴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ኩሳ በበኩላቸው ''በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በሰላም ሰልፈኞች ላይ የተፈፀመው አስነዋሪ ድርጊት ሊኮነን ይገባል'' ብለዋል። ''ድርጊቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለንን  ድጋፍ ይበልጥ እንዲጨምር ያደርገዋል ሲሉ'' ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም የወረዳው አስተዳደር  በሞት ልጃቸውን ላጡ ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የሟች ወላጅ እናት ወይዘሮ አያኔ አሳሮ “ልጄ መንግስትን ለመደገፍ በወጣበት ለህልፈት መዳረጉ ጀግና ነው'' ብለዋል። በተለይም ዶክተር አብይ ደውለው በማፅናናታቸው በውስጣቸው የነበረውን ሐዘን እንዲቀል ማድረጉን ገልፀው፣ ለመንግስታቸው የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል፡፡ የሟች ታላቅ ወንድም አቶ ኦንዶ አያሌው ''የወንድሜ ሞት በዚህ መልኩ መሆን ለመንግስት የማደርገውን ድጋፍ የበለጠ ያጠናክረዋል''ብለዋል። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በአገሪቱ እየታዬ ያለውን የአንድነትና የልማት መንፈስ  ለማጠናከር  የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ  እንደሚያደርጋቸውም ገልፀዋል። ወጣት ዮሴፍ አያሌው በግንቦት ወር 1982 በወላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ ኪንዶ ኮዮ ቀበሌ መወለዱን በቀብር ስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡ በቀብር ስነስርዓቱ ላይ የሟች ወዳጅ ዘመዶች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የወላይታ ዞንና የዳሞት ወይዴ ወረዳ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም