ጥምቀት የአንድነትና የአብሮነት እሴቶችን ለዓለም የምናስተዋውቅበት በዓል ነው- --የሀይማኖት አባቶችና ነዋሪዎች

75

ሶዶ/ዲላ/አርባምንጭ/ሚዛን (ኢዜአ) ጥር 9 / 2012  የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ ይዘቱ ባለፈ የአንድነትና የአብሮነት እሴቶች መገለጫነቱን ለዓለም ህዝብ የምናስተዋውቅበት ነው ሲሉ በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች የሚገኙ የሀይማኖት አባቶችና ነዋሪዎች ገለጹ። የወላይታ ሶዶ፣ ጌዴኦና ጋሞ ዞኖችና የሚዛን አማን ከተማ የሀይማኖት አባቶችና ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቱን ይበልጥ ለማስተዋወቅ እድል ይፈጥሯል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የወላይታ ሃገረ-ስብከት ሥራ አስኪያጅ መላከ ሠላም ቀሲስ ቦክቻ ኦንጋ እንደገለጹት የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ ይዘቱ ባለፈ የአንድነት፣ የመከባበርና የመቻቻል እሴቶቻችን መገለጫ ስለመሆኑ ለዓለም ህዝብ የምናሳይበት ነው።

በዓሉ ይዘቱን ሳይለቅ ለዘመናት የቆየ በመሆኑና በዩኒስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ በመመዝገቡ የዘንድሮ በዓል አከባበር ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

በዞኑ በሁሉም ገጠር ቀበሌዎችና ከተሞች በታቦት ማደሪያ ስፍራዎች  በዓሉን በልዩ  ድምቀትና ስነ- ስርዓት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

በዓሉ በዓለም ቅርስነት ከመመዝጋቡ ጋር ተያይዞ ዘንድሮ አንድነታችንን በማጠናከር በልዩ ድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል "ያሉት ደግሞ በወላይታ ደብረ-መንክራት አቡነ-ተክለሃይማኖት ገዳም ቄስ  መጋቤ ሥርዓት ቀሲስ ተሰማ ሃይለሚካኤል ናቸው፡፡

የዲላ ከተማ ነዋሪ አቶ ደርቤ ጅኖ በበኩላቸው "የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ሰላማችንና አንድነታችን ለዓለም ህዝብ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል" ብለዋል።

በዓሉ ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ፋይዳው ባለፈ የሀገር መልካም ገጽታ ለመገንባት አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል ።

የጌዴኦ ቡርጅና አማሮ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ ኪዳነ ተካ በበኩላቸው በዓሉን በዞኑ በተለየ ሁኔታ በድምቀት ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።

የጉዞ ሂደቱና ጥምቀተ ባህር ስርዓትን ለማድመቅ የሰንበት ተማሪዎች፣ የቤተክርስትያኗ አገልጋዮችና ምዕመናን በልዩ ትኩረት እየተቀሳቀሱ መሆኑን  አመልክተዋል።

የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ አብሮነታችን ለማጠናከርና   የጋራ እሴቶቻችንን ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ አለው" ያሉት ደግሞ የጋሞ ጎፋ ሀገረ-ስብከት ተወካይ ቀሲስ ያዕቆብ ደስታ ናቸው።

ዘንድሮ በዓሉን በልዩ ድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋክዶ ቤተ ክርስቲያን የሸካ፣ ቤንች፣ ሸኮና ምዕራብ ኦሞ ሀገረ ስብከት የሠበካ ጉባዔ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ሊቀጠበብት ቀለመወርቅ አጥናፉ በበኩላቸው የዘንድሮን የጥምቀት በዓል ከወትሮው በተለየ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

"ለበዓሉ ድምቀት ታቦታት ከየቤተ ክርስቲያናቱ ተነስተው ወደ ጥምቀተ ባህሩ ጉዞ ሲያደርጉና በዕለቱ ሲመለሱም ለሚኖረው ስነ ስርዓት ከወትሮው ለየት ያለ መርሀ ግብር ተዘጋጅቷልል" ብለዋል ።

በዓሉ በሰላምና በድምቀት እንዲከበር  ከወጣቶችና ከከተማው ነዋሪዎች የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል ።

" የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያና የዓለም ህዝብ ሀብት ሆኖ መመዝገቡ የሀገር ገጽታን የሚያጎላ ነው"ያሉት ደግሞ   የሚዛን አማን ከተማ የህብረት ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጋሻው አዲስ ናቸው።

በዓሉን ከወትሮ በተለየ በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የየዞኖቹ ፖሊስ መምሪያዎች በበኩላቸው በዓሉ በሰላም እንዲከበር  አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም