ከብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ጎን እንቆማለን --- የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች

89

ሐረር ኢዜአ ጥር 9 /2012  ብሔራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያከናውናቸው ተግባራት እንዲሳኩ የበኩላችንን እገዛ እናደርጋለን ሲሉ በሐረሪ ክልል የሚገኙ የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ገለፁ ። ብሔራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በክልሉ ከሚገኙ የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮችና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ዙርያ ውይይት አካሔዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከተገኙት መካከል አቶ አብዱሰመድ እድሪስ እንዳሉት በክልሉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተከባብረውና ተቻችለው የኖሩ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አልፎ አልፎ የጸጥታ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል ።

ሰላም ማስፈን ከቻልን አገራችን ለሁላችንም በቂ ናት ያሉት አቶ አብዱሰመድ የተዛቡ ታሪኮችን ተነጋግረንና ተመካክረን በማስተካከልና እርቀ ሰላም በማውረድ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማስፈን ይገባናል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያከናውናቸው  ተግባራት ስኬታማ ለማድረግ የበኩሌን ድርሻ አበረክታለው ሲሉ ተናግረዋል።

አባ ገዳ አህመድ ዮሱፍ በበኩላቸው በህዝብ መካከል ምንም ዓይነት ችግር አለመኖሩን በመግለፅ እንደ አገርም ሆነ እንደ ክልል እየተስተዋሉ ያሉት ችግሮች አመራሩ የፈጠራቸው ናቸው የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል ።

በመሆኑም ተደማምጠንና ተመካክረን በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን ሁላችንም የበኩላችንን ማበርከት ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ፖለቲከኞችን የማስታረቅ ስራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ ዘውዱ መልሰው የተባሉ የከተማው ነዋሪ ናቸው ።

የታሪክ ትርክቶችን ሁሉንም ወገን በሚያስማማ መልኩ በሙሁራን ተጠንቶ መስተካከል አለበት ብለዋል ።

የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶችም ኮሚሽኑን ማገዝ ይገባናል ሰሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ መሀመድ ዮሱፍ በበኩላቸው ስህተቶችን እንዲታረሙ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከሩ ረገድ የአገር ሽማግሌዎች ሚናችንን ማጎልበት ይጠበቅብናል ብለዋል ።

ህዝቡ በአገሪቱ ሰላምና አንድነት እንዲጎለብት ሁሉንም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ያስገነዘቡት ደግሞ የእርቀሰላም ኮሚሽኑ አባል ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር ኢድሪስ ናቸው ።

በተለይ የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች አንድነታቸውን በማጎልበት ለሰላም መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

መንግስትም በአገሪቱ ሰዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የህግ የበላይነትን በማስከበር የመሪነት ሚናውን እንዲጫወት ሐጅ ዑመር ጠይቀዋል ።

የኮሚሽኑ አባል ረዳት ፕሮፌሰር መሀመድ ዘካርያ በበኩላቸው  የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የመፍትሄ አካል መሆን ይገባቸዋል ።

የትናንት ስህተትን አርመንና ይቅር ተባብለን በድህነት ላይ መዝመት ይገባናል ሲሉም  አስገንዝበዋል።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንግዳ ማረፍያ ትናንት አመሻሽ ላይ በተከናወነው የውይይት መድረክ ላይ የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አመራርና አባላት ፣ የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም