ሶማሊያ ውስጥ በመኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ ጥቃት ተፈፀመ

66
አዲስ አበባ ጥር 9/2012 በሶማሊያዋ አፍጎዬ ከተማ ውስጥ በቱርክ የግንባታ ኮንትራክተር ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረና በመኪና ላይ የተጠመደ የቦምብ ጥቃት ተፈፀመ። ከሶማሊያ መዲና 30 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው አፍጎዬ ከተማ ዛሬ በተፈፀመው የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት በትንሹ 11 ሰዎች ሳይጎዱ እንዳልቀረ ተነግሯል። ፍንዳታው የተሰማው በከፍተኛ ፍጥነት የሚሄድ መኪና የቱርክ ኮንትራክተሮችና የሶማሊያ ፖሊስ አባላት ምሳ ይመገቡበት ከነበረ ምግብ ቤት ከተጠጋ በኋላ ነው ሲሉ የአገሪቱ ፖሊስ መኮንን ኑር አሊ ለሬውተርስ ነግረዋል። ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም በአካባቢው ተደጋጋሚ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት የሚፈፅመው የአልቃይዳው ክንፍ አል-ሸባብ ሊሆን እንደሚችል መገመቱን መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው። አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉትም የአል-ሸባብ ታጣቂዎች ትናንት ዕለተ ዓርብ ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም አፍጎዬ ከተማ ውስጥ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ ያለውን የሶማሊያ መንግስት ለመጣል የሚንቀሳቀሰው አል-ሸባብ  ባለፉት ጊዜያት በሞቃዲሾና ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለተፈፀሙ ተመሳሳይ የሽብር ጥቃቶች ኃላፊነት ሲወስድ ቆይቷል። በአውሮጳዊያኑ አቆጣጠር 2011 በሶማሊያ የተከሰተውን ረሃብ ተከትሎ ቱርክ የሶማሊያ ዋነኛ ዕርዳታ አቅራቢ አገር ሆናለች። ዘገባዎች እንደሚሉት የቱርክ መንግስት ተቀናቃኞቿ የሆኑት ሳዑዲና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬት አገራት እያደረጉት እንዳለው በምስራቅ አፍሪካ የራሱን ተፅእኖ ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ ነው። በአሁኑ ወቅትም የቱርክ ኮንትራክተሮች በሶማሊያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ድጋፍ እያደረጉ ናቸው። ባለፈው ወር በሞቃዲሾ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ኬላ ላይ በተፈፀመና ለ90 ንፁሃን ሰዎች ሞት ምክንያት በሆነው መሰል የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ቱርካዊያን ይገኙበታል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም