የወሎና አሶሳ ዩኒቨርሲቲዎች የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራ ሊጠቀሙ ነው

79

ደሴ አሶሳ (ኢዜአ) ጥር 9 /2012  የወሎና አሶሳ ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊና ደህንነቱ የተረጋገጠ የመማር ማስተማር ሒደቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ይረዳ ዘንድ የደህንነት ካሜራና ዲጂታል መታወቂያ ጥቅም ላይ ለማዋል መዘጋጀታቸውን አስታወቁ ።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አማረ ምትኩ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎችና ለሰራተኞች ዲጅታል መታወቂያ አዘጋጅቷል ።

ዲጂታል መታወቂያው ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር ተመሳስለው በመግባት ችግር የሚፈጥሩ ህገወጦችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል ።

በያዝነው ዓመት በደሴ ካምፓስ በተማሪዎች መካከል በተደጋጋሚ ግጭት ቢፈጠርም ከአካባቢው ማህበረሰብና ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገርና አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ የመማር ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል እንደተቻለ ገልፀዋል ።

ነገር ግን አሁንም በተማሪዎች በኩል የተለያዩ ስጋቶች በመኖራቸው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ለመመፍጠር የዲጅታል መታወቂያ ማዘጋጀትና የደህንነት ካሜራ መግጠም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።

የደህንነት ካሜራው የሚገጠመው በዩኒቨርሲቲው ግቢ ዋና ዋና የተማሪዎች መተላለፊያ ቦታዎች፣ ለእይታ ምቹ በሆኑ የአጥር አካባቢዎችና ሌሎች አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ላይ ነው ተብሏል ።

የደህንነት ካሜራው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተገጥሞ ስራ እንዲጀምር ውሳኔ መተላለፉንም ዶክተር አማረ ተናግረዋል ።

የደህነት ካሜራውና ዲጂታል መታወቂያው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደቱን ተጠናክሮ እንዲቀጥል እገዛ ያደርጋሉ ተብሎ እንደታመነባቸው ከዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ገለፃ ለመረዳት ተችሏል ።

ዩኒቨርሲቲው በግቢው ውስጥ  ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ባደረጉ 335 ተማሪዎች፤ የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን ላይ ባለፈው ወር እርምጃ መውሰዱን ኢዜአ በወቅቱ መዘገቡ የሚታወስ ነው ፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የአሶሳ ዩኒቨርስቲም ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት መጠናከር እንዲያግዘው የደህንነት ካሜራ ለመጠቀም መዘጋጀቱን አስታውቋል ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም በሰጡት መግለጫ ዩኒቨርስቲው በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማሩን ሒደት ለማደናቀፍ ከውስጥና ከውጭ የተለያዩ ሙከራዎች አጋጥመውት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እንዲከሽፍ ተደርጓል።

አሁን በዩኒቨርሲቲው እየታየ ያለው አንፃራዊ ሰላም ለማጠናከር በቅርቡ የደህንነት ካሜራ ተገጥሞ በመጪው የካቲት ወር ለአገልግሎት እንዲበቃ ይደረጋል ብለዋል ።

ዩኒቨርሲቲው ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር የመማር ማስተማር ሒደቱን ለማስተጓጎል ጥረት አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ 65 ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሰራተኞች በህግ እንዲጠየቁና የዲስፕሊን እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረጉንም ዶክተር ከማል ተናግረዋል ።

በሁከትና ብጥብጡ ተጠያቂ ከተደረጉት መካከል 50ዎቹ ተማሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሰራተኞች ናቸው ተብሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም