በደቡብ ክልል የመልካም አስተዳደርና የፍትሃዊነት ጥያቄዎች የሕዝቡን አብሮነት ተፈታትነዋል…የክልሉ ምሁራን

58
ሆሳዕና፤ ጥር 9 /2012 (ኢዜአ) በክልሉ የዜጎች ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በአግባቡ አለመረጋገጥ ለአደረጃጀት ጥያቄዎች መነሳት ምክንያት በመሆኑ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ የደቡብ ክልል ተወላጅ ምሁራን አመለከቱ። በሆሳዕና እየተካሔደ ባለው የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ጉባኤ ላይ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የመጡት ዶክተር አጥናፉ ገብረመስቀል እንዳሉት የህዝቦችን አብሮነት እየሸረሸረ የመጣው የመልካም አስተዳደር እና የፍትሀዊ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ችግር ነዉ። በመሆኑም አብሮነትና አንድነቱን ማጠናክሮ ማስቀጠል የሚቻለው የህዝብን ፍላጎት በመረዳት ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን በማስፈንና ለመልማት ጥያቄያቸው መልስ መስጠት ሲቻል እንደሆነ ተናግረዋል። የአደረጃጀት ለዉጥ ማምጣት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚፈጥረዉ ተጽእኖ እንደሌለ የተናገሩት ዶክተር አጥናፉ ተሳስሮ የኖረዉ ህዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ፍትሃዊ ለማድረግ መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ሀገሪቱ ካላት ሀብት ለህዝቡ በማድረስና የወጣቶችን ተጠቃሚነት በማጠናከር የክልሉን የአደረጃጀት ጥያቄ መመለስ እንደሚቻል የተናገሩት ደግሞ ከደቡብ ክልል ጥናትና ምርምር ኢንስቲቱዩት በመድረኩ የተገኙት ዶክተር አብርሀም አላኖ ናቸዉ፡፡ በክልሉ በከተማ ደረጃ 18 ነጥብ5 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ስራ አጥ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዉ በዚህም የተነሳ ወጣቶች በተለያየ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ተሰባስቦ የተለያዩ ጥያቄዎችን እንዲያነሳ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል። ለመሰል የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ፍትሀዊ ምላሸ ባለመሰጠቱም በክልሉ ህዝቦች አብሮነት ላይ ተግዳሮት መሆኑን ተናግረዋል። ፍትህዊ ተጠቃሚትን በማሳፋት የህዝቡን አብሮነት ማስቀጠል እንደሚገባም ዶክተር አብርሃም ገልጸዋል። ሌላኛው የሚዛን ቴፒ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸዉ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ያለዉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ለሀገር ሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ተጠቃሚነት ላይ ቢሰራ ለሀገርም ለወገንም ጠቀሜታዉ የጎላ መሆኑን አስታዉቀዋል፡፡ የውይይት መድረኩ በትልንት ውሎው በክልሉ መንግስት የተጠናው የአደረጃጀት ጥናት ዙሪያ በቀረበ ጽሁፍ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ዛሬ ይጠቃለላል ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም