ከመጠጥ ሱስ ባለቤቷን ለማውጣት የቀመመችው ፈሳሽ ወህኒ አወረዳት

1044

ጥር 8/2012 (ኢዜአ) ሜክሲኳዊቷ  ከመጠጥ ሱስ ባለቤቷን ለማውጣት የቀመመችው ፈሳሽ ለእስር እንደዳረጋት  ተነገረ።

የመጠጥ ሱስ አልለቅ ያላቸው ከሱሱ ዛር ለመለየት የተለያዩ ዘዴዎችን ይተገብራሉ።

ታዲያ በርካቶቹ ከተጣባቸው ሱስ ለመገላገል በሚል የሚጠቀሟቸው ብልሃቶች አንዳንዴም አስገራሚ አልፎ አልፎ ደግሞ እንዲህም አለ እንዴ የሚያስብሉ ድርጊቶችን ይከውናሉ።

ታዲያ በርካቶቹ ከሱስ ለመገላገል በሚል የሚጠቀሟቸው ብልሃቶች አንዳንዴም አስገራሚ አልፎ አልፎ ደግሞ እንዲህም አለ እንዴ የሚያስብሉ ድርጊቶችን ሲፈጸሙ እናያለን።

ከዚሁ ጋር የተያያዘ አንዲት የሜክሲኮ ሴት በመጠጥ ፍቅር የናወዘ ባለቤቷን ከገባበት ሱስ ለማላቀቅ የተጠቀመችውን ብልሃት ጉድ ስሙ ሲል ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።

ጆሴ ብሪያን በሚል የመዝገብ ስም የሚታወቀው ባለቤቷ የተጣባውን የመጠጥ ሱስ ለማስቆም ከተለያዩ የኢንተርኔት ገፆች ጋር ምክር ስትፈፅም እንደከረመች የተነገረላት ሜክሲኳዊቷ ሚቼል ኤን ከጉሎ ዘይት እና ፕልም ከተሰኘ ፍሬ የተዘጋጀ ውሁድ ፈሳሽ ቀምማ ማዘጋጀቷ ነው የተነገረው።

በአንድ ወቅት ታዲያ ይህቺው ሜክሲኳዊት ያዘጋጀችውን ፈሳሽ ነገር ባለቤቷ በሚጠጣው ቢራ ውስጥ ጠብ በማድረግ ትሰጠዋለች፤ ከዚያም ከምንም ነገር በላይ የሚወደውን ቢራ ወደ ማጣጣም የገባው ባለቤቷ ቢራው እንግዳ የሆነ ጣዕም እንዳለው ቢገምትም ጭልጥ አድርጎ ይጠጣዋል።

‘አንድ አይቀመጥም፤ ሁለት አይጨለጥም’ እንዲሉ ጠጪዎች። ጉዱ የመጣው ከቆይታ በኋላ ሆነ እንጂ።

በመጠጡ ውስጥ ተቀምሞ የተሰጠው ከጉሎ ዘይትና ፕልም ፍሬ የተዘጋጀው ፈሳሽ ቀስ በቀስ ስራውን መስራት ይጀምራል።

ዘና ተብሎ የተጨለጠው ቢራ ግለሰቡን ወደ ታች ይለው ጀመር፤ ወዲያውኑም መፀዳጃ ቤት ደጋግሞ እንዲጎበኝ አደረገው።

ይህንኑ ሁኔታ ቆማ ስትታዘብ የነበረችዋ ባለቤቱ ቢራው አላርጂክ እንደሆነበት ትነግረዋለች።ማን ሊሰማት አሁንም አሁንም ወደ ታች በሚል ጥድፊያ ውስጥ ያለ ሰው ወትሮስ ማንን ሊሰማ።

ነብስ ግቢ ነብስ ውጪ ሆነ። በዚህ ጊዜ ሚቼል ኤን ድንጋጤ ውስጥ ትገባለች። ባል በሰውነቱ ውስጥ ያለ ፈሳሽ እያለቀ በመምጣቱ ተዳከሞ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወሰደ።

የባሏን የመጠጥ ሱስ አባርራለሁ ብላ አስባ የነበረች ሴት በቅፅበት ወደ አልታሰብ ጭንቀት መዘፈቋን ዘገባው አብራርቷል።

የሆስፒታሉ ሃኪሞች ብርያን አንዳች ነገር ተመግቦ ወይም ጠጥቶ ለችግር መዳረጉን እንደደረሱበት የተረዳችው ባለቤቱ የፈፀመችውን አንዳችም ሳትደብቅ ተናዘዘች።

ከዚያም እሷ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ ዘብጥያ ስትወርድ ባለቤቷ ደግሞ ለተጨማሪ ህክምና ሆስፒታል ውስጥ እንዲቆይ መደረጉን የዘገበው ኦዲቲ ሴንትራል ብሪያን በሆስፒታል አልጋ ላይ ሆኖ ቢራ እርም ማለቱን መናገሩን አስነብቧል።