የሊቢያ ታጣቂ ቡድን መሪ ካሊፋ ሃፍጣር ግሪክ እንደሚገኙ ተገለፀ

72
ጥር 8/2012 (ኢዜአ) ጠንካራው የሊቢያ መንግስት ተቀናቃኝ መሪ ካሊፋ ሃፍጣር መቋጫ ያላገኘውን የሊቢያ ቀውስ ለማስቆም በዚህ ሳምንት በርሊን ላይ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ስብሰባ ጉዳይ ለመምከር ከግሪኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኒኮስ ደነዲያስ ጋር በአቴንስ መገናኘታቸውን ቢቢሲ አስነበበ፡፡ ከወደ ግሪክ የሚወጡ ሪፖርቶች አጀንዳዎቹ በምን ጉዳይ እንደሚያተኩሩ ያሉት ነገር ባይኖርም፤ ጀኔራል ካሊፋ ሃፍጣር የግሪኩን ጠቅላይ ሚኒስቴር ኪሪያኮስ ሚፆታኪስን ጨምሮ ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ግሪክ በጀኔራል ሃፍጣር የሚመራውን ሃይል በማግለል በቅርቡ በቱርክ እና  በመንግስታቱ ድርጅት በሚደገፈው የሊቢያ መንግስት መካከል የተደረሰውን ስምምነት አጥብቃ እንደምትቃወምም ዘገባው አትቷል፡፡ ስምምነቱ በሊቢያና በቱርክ መካከል የሜዲትራኒን ባህር ዳርቻን በመከፋፈል በቀጠናው የሚካሄደውን የተፈጥሮ ነዳጅ ፍለጋ ላይ አንድምታ እንዳለውም በዘገባው ተገልጿል፡፡ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሂኮ ማስን መቀመጫውን ቤንጋዚ አድርጎ ከሚንቀሳቀሰው የታጣቂ መሪ ጀኔራል ካሊፋ ሃጣታር ጋር ከተገናኙ በኋላ ከመንግስታዊ ተቀናቃኛቸው ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማደርረግ ፍላጎት እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በማከልም የሊቢያ ታጣቂ ሃይሎች መሪ ካሊፋ ሃፍጣር በዚሁ ሳምንት ቀጣይ እሁድ ላይ በጀርመኗ ከተማ በርሊን ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የሰላም ድርድር ላይ እንደሚገኙ ፍንጭ ሰጥተዋል ማለታቸውን ቢቢሲ በአፍሪካ ገፁ እወቁልኝ በሏል፡፡ የሊቢያው የጦር አዛዥ ከሊፋ ሃፍጣር በመንግሥታቱ ድርጅት እውቅና ከተሰጠው የሃገሪቱ መንግሥት ጋር የተኩስ አቁም ለማድረግ የተዘጋጀውን ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ሳይፈርሙ ከሞስኮ ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም