በፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ ሊካሄዱ የነበሩ ጨዋታዎች ተራዘሙ

62
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሊደረጉ የነበሩ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ተራዘሙ። በሃዋሳ ስድታዲየም ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና፤ ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት  ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ መርሃ-ግብር ወጥቶላቸው ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታዎቹ ከነገ በስቲያ እንደሚካሄዱና ቦታዎቹ መቀየራቸውንም ለኢዜአ አሳውቋል። በዚህም መሰረት ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት፣ ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ። በአዲስ አበባ ስታዲየም ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ደደቢት ከአርባምንጭ ከተማ የሚያደርጉት ተስተካካይ ጨዋታ በወጣለት መርሃ-ግብር መሰረት የሚከናወን ይሆናል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ28ኛ እና በ29ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ የቀን ለውጥ ማድረጉ የሚታወስ ነው። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ጅማ አባ ጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 48 ነጥብ፣ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ መቀሌ ከተማ በ46 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ኢትዮ-ኤሌትሪክ፣ አርባምንጭ ከተማ እና መውረዱን ያረጋገጠው ወልዲያ ከተማ በቅደም ተከተል ከ14 እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት ናይጄሪያዊው የጅማ አባጅፋር ተጫዋች ኦኮኪ አፎላቢ በ17 ግቦች እየመራ ሲሆን፣ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና የኢትዮ- አሌትሪኩ ጋናዊ ተጫዋች አልሃሰን ካሉሻ በተመሳሳይ 11 ግቦች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም