በመሻሻል ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ ቅናሽ እንጂ ጭማሪ አላደረገም

152

ጥር 7/ 2012 ኢዜአ በመሻሻል ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ የታክስ ቅናሽ እንጂ ምንም ዓይነት ጭማሪ እንደማያደርግ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከአሁን በፊት የነበረው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ከ1995 ዓም ጀምሮ ለረዥም ጊዜ የቆዬ በመሆኑ ምክንያት ከወቅቱ ጋር የማይጣጣም ነው።

በዚህም ምክንያት ማሻሻያው እንደ ጨው፣ስኳር፣ዘይትና መሰል የህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ፍጆታዎች ላይ የታክስ ቅናሽ በማድረግ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከአሁን በፊት አስከ 80 በመቶ ታክስ ተጥሎባቸው የነበሩ በቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎች እንደ ልብስ ማጠቢያ ማሽን እና 30 በመቶ ታክስ ተጥሎባቸው የነበሩ የሳህን ማጠቢያ ማሽኖችም ከታክስ ነፃ ያደረገ ነው።

ታክሱ የስነ ጥበብ ዘርፉን ለማበረታታት በማለትም ከአሁን በፊት 40 በመቶ ታክስ ተጥሎባቸው የነበሩ እንደ ቪዲዮ ካሜራ፣ቴሌቪዥን፣ዴክና የመሰሳሰሉት ምርቶችም በአዲሱ አዋጅ የታክስ መጠናቸው ወደ 10 በመቶ ዝቅ ተደርጓል።

የግብርና ውጤቶችን ተጠቅመው በአገር ውስጥ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ እንደ ቢራና ወይን አምራቾች ላይም ይጣል የነበረውን 50 በመቶ ታክስ ወደ 30 በመቶ ዝቅ ብሏል ሲሉም አብራርተዋል።

በመሆኑም የታክስ ጭማሪ የሚደረግባቸው የጤና ችግር የሚያመጡ እንደ ሲጋራና መሰል ምርቶች፣ በአካባቢ ላይ ብክለትን የሚያደርሱ እንደ አሮጌ ሜኪኖችና መሰረታዊ ጥቅማቸው የጎላ ያልሆኑ የቅንጦት እቃዎች ላይ በመሆኑ መንግስትንም ህብረተሰቡንም የሚጠቅም ነው ሲሉ አቶ ሃጂ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም