በትግራይ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው የክልሉ ተወላጆች ገለፁ

95
አዲስ አበባ፤ጥር  7/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት የሚታየው የዜጎች የፖለቲካ ነፃነት እጦት ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው በአዲስ አበባ የሚኖሩ አንዳንድ የክልሉ ተወላጆች ገለፁ። በሌላ በኩል በትግራይ የሚንቀሳቀሱት የብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ እና የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ፓርቲዎች የፖለቲካ ተግባራቸውን በነፃነት እያከናወኑ መሆኑን ይናገራሉ። ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት በትግራይ ክልል የፖለቲካ ነፃነት የለም፤ ህዝቡ በከፍተኛ አፈና ውስጥ ነው። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የቀድሞ የሕውሓት ታጋይ ሌተናል ኮነሬል ፍሰሃ በረሄና አቶ ሙዑዝ ገብረሕይወት፤ የትግራይ ሕዝብ የፖለቲካ ነፃነት የተገደበና ሃሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱ የታፈነ መሆኑን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢህአዴግ  አሠራር  ታግሎ የጣለው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ በመጣሱ እንዲሁም ሃሰብን የመግለጽ ነፃነቱ ባለመከበሩ ቢሆንም አሁን ችግሩ በክልሉ እንዳለ ነው የገለጹት። በመሆኑም የለውጥ ሃይሉ በሀገሪቱ የጀመረውን እውነተኛ ዴሞክራሲን የማስፈን እንቅስቃሴ በትግራይም ይተገበር ዘንድ በትጋት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል። ከለውጡ በፊት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የነበረው አፈና ወደ ትግራይ ሕዝብ መሸጋገሩንም አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ። በቅርቡም ሕውሓት 'ራሴን ከብልጽግና ፓርቲ ነጥያለሁ' ብሎ ባወጣው መግለጫ ላይ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያስጠነቀቀበት ሁኔታ አንዱ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ። የትግራይ ሕዝብ እና ወጣት ያለበትን አፈና 'ይብቃቹ' በማለት ነፃነቱን እንዲያስከብር አስተያየት ሰጪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል። መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ከአፈና ለማውጣት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን በማገዝና ለሕዝቡ በመድረስ የሕግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚገባውም ጠይቀዋል። በሌላ በኩል መሰረታቸውን በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አድርገው የሚንቀሳቀሱት የብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ እና የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ፓርቲዎች በክልሉ የፖለቲካ ምህዳሩ የጠበበበት ሁኔታ የለም ይላሉ። የብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ኪዳነ አመነ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ፓርቲያቸው በትግራይና ከትግራይ ውጪ በሚገኙ ክልሎች ለመወዳደር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያካሄደ ነው። ፓርቲያቸው እያካሄዱት ካለው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት አፈና እየገጠማቸው እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት። በክልሉ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ነፃነት መኖሩን በማውሳት። ከአቶ ኪዳነ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ያላቸው የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አሉላ ኃይሉ፤ ፓርቲያቸው በቅርቡ ባካሄደው ሕዝባዊ መድረክና የድርጅቱ ጉባኤ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች አለተጽኖ ያሰቡትን እያከናወኑ ነው  ብለዋል። ይህም በክልሉ ላለው የፖለቲካ ምህደር የተሻለ መሆን ማሳያ ነው ይላሉ። የፓርቲዎቹ አመራሮች የወደፊቱን የሚወስነው በቀጣዮቹ ወራት በሚካሄደው የምርጫ እቅስቃሴ ላይ ይሆናል ይላሉ። ኢህአዴግ ራሱን አክስሞና አጋር ድርጅቶቹን ይዞ የብልጽግና ፓርቲን መመሥረቱና አዲስ ውህድ ፓርቲ መስርቷል፤ ይህም በምርጫ ቦርድ እውቅ ተሰጥቶታል። ይሁንና ከግንባሩ መስራቾች አንዱ የሆነው ሕውሓት ራሴን አክስሜ አዲሱን የብልጽግና ፓርቲ አልቀላቀልም ብሎ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም