ገርሁ ስርናይ የኢትዮ-ኤርትራ ሰላምን ያጣጣመችው ከተማ

አክሱም ጥር 7/ 2012 (ኢዜና) በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የገርሁ ስርናይ ከተማ ነዋሪዎች የልማት ጥያቄዎቻቸው  ምላሽ እያገኙ መሆኑን የከተማዋ ሥራስኪያጅ ገለጹ። ሥራስኪያጁ አቶ ተክላይ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከተማዋ በጸጥታ ረገድ የነበራት ስጋት አገሮቹ መካከል  በተደረሰው ስምምነት በመወገዱ ፊቷን ወደ ልማት መልሳለች። ከተማዋ በኮንስትራክሽንና ንግድ ዘርፎች መነቃቃት አሳይታለች ያሉት ሥራስኪያጁ፣ የትግራይ ክልል መንግሥት በመደበው 125 ሚሊዮን ብር በጀት ችግሮቿን የሚያቃልሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል። ከነዚህም የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርን በዘላቂነት የሚፈታ ግድብ እየተገነባ መሆኑን በአብነት አቅርበዋል። ግንባታው 90 በመቶ የደረሰው የግድቡ ግንባታ የነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ አቅርቦት እንደሚያቃልል ተናግረዋል። አሁን ያለውን የከተማዋን 39 በመቶ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ወደ 90 በመቶ የሚያሳድገው ግድብ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለዋል። ነዋሪዎቹ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት ሦስት የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮችን ጠግነው ለአገልግሎት ማብቃታቸው አስታውቀዋል። የከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ጠጠር ለማልበስ እየተሰራ መሆኑን አቶ ተክላይ አስረድተዋል። “በሁለቱም አገራት በተፈጠረው ተስፋ ሰጪ የሰላም ሁኔታ ድንበር አካባቢዎች ያሉ ከተሞች እድገት እያሳዩ ነው። የገርሁ ስርናይ ከተማን እድገት ለማስቀጠልና የመሰረተ ልማት ሥራዎች ለሟሟላት በትኩረት እንሰራለን'' ብለዋል። የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አጀብ ለምለም በሁለቱ አገሮች መካከል በነበረው አለመግባባት ላለፉት 20 ዓመታት በስጋት ኖሬያለሁ ይላሉ። ''የመሰረተ ልማት እጥረት ለመቅረፍ ህዝቡ ባለው አቅም ድጋፍ እያደረገ ነው፤ እኔም የመብራት መቆራረጥ ችግርና የትራንስፎርመር እጥረት ለመቅረፍ 12 ሺህ ብር በማዋጣት ዜግነታዊ ግዴታዬን ተወጥቻለሁ'' ብለዋል። በከተማዋ የ03 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተስፋአለም ገብረመስቀል እንዳሉ የከተማዋን የመሰረተ ልማት አውታሮች ችግሮች ለማቃለል በትብብር መስራትያስፈልጋል፡፡ የከተማውና የአካባቢው ማህበረሰብ ባወጣው ገንዘብ የእገላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ተገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱ ይታወቃል። ገርሁ ስርናይ በትግራይ ክልል አህፈሮም ወረዳ የምትገኝ ከተማ ናት።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም