ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በዋሽንግተን ያካሄዱት ውይይት የጋራ መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

89

ጥር፤ 7/2012 ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ላለፉት ሁለት ቀናት በኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ላይ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ያካሄዱት ውይይት የጋራ መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ።

የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውሃ ሃብት ሚኒስትሮች እና የልዑካን ቡድኖቻቸው በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ባካሄዱት ውይይት ላይ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስቴቬን ሙንሺን እና የአለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ  በታዛቢነት ተሳትፈውበታል።

በዚህ ስብሰባ ላይ ከዚህ ቀደም በሶስቱ አገራት ዋና ከተሞች እና በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄዱትን ድርድሮችና እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን የተመለከተ ሪፖርት ቀርቧል።

አገራቱ እስካሁን በተደረጉ ድርድሮች በልዩነት የሚያነሷቸውን ሃሳቦች በሚመለከትም  በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ መፍታት በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ ተወያይተው የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

የግድቡ የውሃ ሙሊት ስራ የወንዙን የውሃ መጠን ባገናዘበና የታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት በማያስከትል መልኩ መከናወን እንዳለበት መግባባታቸውን ነው በጋራ መግለጫቸው ያመላከቱት።

ሙሌቱ በክረምት ወቅት የሚከናወን ሲሆን፤ ሐምሌና ነሃሴ ደግሞ ዋነኛ የሙሌት ስራ ማከናወኛ ወራቶች ናቸው ተብሏል።

ነገር ግን ወቅታዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ የሙሌት ስራው እስከ መስከረም ሊቀጥል እንደሚችልም በጋራ መግለጫው ተጠቁሟል።

በውሃ ሙሌት ጊዜም ሆነ ከሙሌት በኋላ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ድርቅ ቢያጋጥማቸው የወንዙ ፍሰት ምን መምሰል እንዳለበት አገራቱ ተወያይተው መግባባት ላይ ደርሰዋል ነው የተባለው።

የግድቡ አጠቃላይ ሃይል የማመንጨት ስራ የወንዙን የውሃ መጠንና የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚገጥማቸውን የአየር ጠባይ ባገናዘበ መልኩ እንዲከናወን መግባታቸውንም መግለጫው ይፋ አድርጓል።

በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ  ድርቅ ቢከሰት አገራቱ በመተባበር መተማመን እና በኃላፊነት መንፈስ ተቀራርበው ለመስራት መስማማታቸውም በመግለጫው ተመላክቷል።

በመጨረሻም የአገራቱ  የደረሱበትን ስምምነት ለማጠቃለል  እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በመጪው ጥር 28 እና 29 በዋሽንግተን ዲሲ ለመገናኘት ወስነዋል።

በመካከል ባለው ጊዜም የሶስቱም አገራት የህግ ባለሙያዎች የተወከሉበት ቡድን በህግ ማዕቀፎቹ ላይ የጋራ ምክክር እንደሚያካሄድ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም