የግብፅ ፓርላማ ተጥሎ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ ሶስት ወራት አራዘመ

102

ኢዜአ፤ ጥር 6/2012 የግብፅ ፓርላማ ቀደም ሲል በሃገሪቱ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ ጥሎት የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደገና ለሶስት ወራት እንዲራዘም መወሰኑን አንድ የፓርላማ አባልን ዋቢ በማድረግ ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

ፕሬዚዳንታዊ ድንጋጌን መሰረት ያደረገው የግብፅ ፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እአአ ከጥር 27/2020 ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ወራት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኑን የግብፅ የፓርላማ እንደራሴው ሞሃመድ ሃሚድ ለዢንዋ መናገራቸውንም ዘገባው አክሏል፡፡

ውሳኔ በተላለፈበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረትም የሃገሪቱ ወታደራዊና የፖሊስ ሃይል ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና በመላ ሃገሪቱ ደህንነትን ለመጠበቅ ያስችላሉ ያሏቸውን አስፈላጊ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው መነገሩን ዘገባው አመልክቷል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመጀመሪያ ጊዜ ገቢር የተደረገው እ.አ.አ በሚያዚያ 2017 በሁለት አብያተ ክርስቲያናት ላይ በተፈፀመ የቦንብ ፍንዳታ 47 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ሲሆን ይኸው አዋጅም እስካሁን ድረስ ገቢራዊነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡

የግብፅ የፀጥታ ሃይሎች በሃገሪቱ ገጠራማ እና ሰሜናዊ የሰነዓ በርሃ አካባቢ ያሉ የሽብር ቡድኖችን ለመዋጋት በሚል እ.አ.አ. ከየካቲት 2018 ጀምሮ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

አቡ ሃሚድ የተሰኙ ግለሰብ በማከልም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም የሚመለከታቸው አስፈፃሚ ተቋማት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የህግ መሳሪያ አድርገው እንዲጠቀሙበት ስለሚያግዛቸው ሁሉም የፓርላማ አባላት ድምፀ ውሳኔ አስተላልፈዋል ብለዋል፡፡

በግብፅ ህገ-መንግስት መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለማደስ የፕሬዚዳንታዊ ውሳኔዎች ለፓርላማ ቀርበው መፅደቅ  እንደሚኖርባቸውም ሲ ጂ ቲ ኤን በዘገባው ጠቁሟል፡፡