“አብሮነት ከጋሞ እስከ ጎንደር “ ጉዞ ተጀመረ

78
ዓርባ ምንጭ፤ ጥር 6/ 2012 (ኢዜአ) የጋሞ ዞን አባቶችና ወጣቶች የተሳተፉበት አገር አቀፍ የሰላም ጉዞ ዛሬ ተጀመረ። ጉዞው የተዘጋጀው “አብሮነት ከጋሞ እስከ ጎንደር “በሚል መሪ ቃል ነው። የጋሞ ዞን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሰግድ ተረፈ ለኢዜአ እንደገለጹት የጉዞው ዓላማ የጋሞ ዞን የሰላምና የፍቅር ገጽታን ለሌሎች ወገኖች ለማካፈል ነው፡፡ ከጥር 6 እስከ 14 ቀን 2012 በሚቆየው መርሃ ግብር መነሻውን ዓርባ ምንጭ በማድረግ አዲስ አበባና ባህር ዳር ከተሞችን አቋርጦ ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማን መድረሻ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ። ተጓዦቹ በነገው ዕለት የአንድነት ፓርክን እንደሚጎበኙና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ጋር ቆይታ እንደሚኖራቸው አስታውቀዋል ። ጉዞው 150 የልዑካን ቡድን አባላት ያሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል። ተጓዦቹ በሚደርሱባቸው ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች የሰላምና ፍቅርን ጠቀሜታ  የሚያሳዩበት  ምክር እንደሚሰጡ አቶ አሰግድ ጠቁመዋል፡፡ የጋሞ አባቶች ተወካይ ካዎ ታደሰ ዘውዴ በበኩላቸው በጋሞ አካባቢ ግጭት ከመከሰቱ በፊት ማብረድ የቻለና ከተከሰተ በኋላም  ቂም የለሽ እርቅ በመፈጸም የህዝቡን ሰላም ሲያረጋግጥ የቆየ ጠንካራ የባህል ስርዓት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ "ስርዓቱ በመኖሩ የአከባቢው ነዋሪ ብሔር ብሔረሰቦች በመከባበር፣ በመፈቃቀር፣ በመቻቻልና በአብሮነት ለረጅም ዓመታት ቆይተዋል" ብለዋል፡፡ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባለፈው ዓመት በዓርባ ምንጭ ከተማ ሊፈጸም የነበረ ግጭትን እርጥብ ሳር በመያዝ አባቶች ማብረዳቸውን አስታውሰዋል፡፡ "እኛም ኢትዮጵያዊ ለዛ ያለውን ልምድ ለሌሎች ወገኖቻችን በማካፈል ለአገራችን ሰላም የበኩላችንን ለመወጣት ጉዞውን  አዘጋጅተናል "ብለዋል፡፡ ለጉዞው ሰላማዊነት የሰላም ሚኒስቴር እንዲሁም የደቡብ፣ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ካዎ ታደሰ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም