በጎንደር የባህል ሳምንት እየተከበረ ነው

63
ጥር 6 ቀን 2012 በጎንደር ከተማና አካባቢው የጥምቀትን በዓል ተመርኩዞ የባህል ሳምንት ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ነው። ሳምንቱ ባህላዊ ክዋኔዎችንና እሴቶችን ለበዓሉ በሚመጡ የውጭ ቱሪስቶች በማቅረብ የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም መዘጋጀቱን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል። ከበዓሉ አንድ ሳምንት ቀድሞ በሚካሄደው ሳምንት ከትናንት ማምሻው ጀምሮ ትዕይቶችን በዋና ዋና ጎዳናዎችና በተመረጡ አካባቢዎች ማሳየት ተጀምሯል። የመምሪያ ኃላፊው አቶ አስቻለው ወርቁ እንዳሉት የሳምንቱ ዋና ዓላማ  የከተማውንና አካባቢውን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅና የውጭ ቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ያለመ ነው። ኪነ-ጥበባዊና ባህላዊ ክዋኔዎችን ለእይታ በማቅረብ ባህሉን ለዓለም ለማስተዋወቅ እንደሚያስችል ተናግረዋል። እንዲሁም ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች በፌስቲቫል መልክ ለቱሪስቶችና ከሌሎች አካባቢዎች ለሚመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚቀርብ  ኃላፊው አስረድተዋል። በተጨማሪም የከተማዋንና የአካባቢውን ሕዝብ ለጥምቀት በዓል ልዩ ትኩረት በመስጠት በድምቀት እንዲያከብር መነቃቃትን ለመፍጠር እንደሆነም  ተናግረዋል። በትዕይንቱ ከ200 በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉና በዚህም ባህላዊና ጥንታዊ ክዋኔዎች የአካባቢውን ታሪክንና ባህልን በጠበቀ መልኩ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ከተማ ነዋሪው ወጣት ኪሩቤል መንግሥቴ "ባህላዊ ትርዒቱን ለማሳየት የሚያስችሉ የተለያዩ አልባሳት፣ ባህላዊና የነገሥታት መገልገያ እቃዎች፣ ባህላዊ ምግብና መጠጦች አስቀድመን እንዲሟሉ አድርገናል" ብሏል፡፡ የፋሲል ቤተ መንግሥትን ለሚጎበኙ የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችም "ሕይወት በአብያተ መንግሥት" ምን ይመስል እንደነበር በማሳየት ከግብረ ህንፃው ተጨማሪ ታሪክና ትውፊቱን  እያሳዩ መሆናቸውን አመልክቷል። "በየወረዳዎቹ የተለያዩ የአጨፋፈር፣ የአለባበስና የሽለላ አይነቶች አሉ። እኛም በአርማጭሆ አካባቢ ያለውን የሳንኪ የአጨፋፈር ስልት ለማሳየት መጥተናል" ያለው ደግሞ ከታች አርማጭሆ ወረዳ የመጣው ወጣት ግዛቸው አባይ ነው፡፡ ሳምንቱ የአካባቢውን ባህል ለሌሎች ከማሳወቅ ባለፈ ለራሱ አቅም ማጎልበቻና የማያውቀውን ባህልና ታሪክ ለማወቅ እንደሚያስችለው ተናግሯል፡፡ ዝግጅቱ  በጎንደር ከተማና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ካሉ ወረዳዎች የተወጣጡ የባህል ቡድኖች አባላት እንደሚያቀርቡት ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም