የአንበጣ መንጋ በምስራቅ አፍሪካ ስጋት ፈጥሯል

56
ኢዜአ ጥር 6 ቀን 2012 የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ በምስራቅ አፍሪካ አገራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚሰራው ስራ ላይ ከፍተኛ አደጋ መጋረጡን የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት አስታወቀ። ድርጅቱ አገራቱ አፋጣኝ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸውም አመልክቷል። የመንጋው በከፍተኛ ሁኔታ መዛመት በኢትዮጵያና በአጎራባቾቿ ሱዳን፣ ኤርትራና ኬንያ ከፍተኛ ስጋት እንደሆነ ተጠቁሟል። የአካባቢው አገራት በሰብል ምርትና የግጦሽ ሳር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያደርስ የመከላከል አቅማቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ማጠናከር እንዳለባቸውም ነው ያሳሰበው። የአየን ንብረት ለውጥ የአንበጣ መንጋው በብዛት እንዲራባና በፍጥነት እንዲዛመት አድርጎታል። ያልተለመደው የአየር ጠባይና እየጣለ ያለው ዝናብ ለአንበጣው መራባት ምቹ ሁኔታን በመፍጠሩ የስጋቱን መጠን ከፍ እንዲል አድርጎታል ተብሏል። በኬንያና በሶማሊያ በኩል እየገባ ያለው የአንበጣ መንጋ ወደተለያዩ አካባቢዎች በከፍተኛ ፍጥነት የመዛመት ዕድሉ ሰፊ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ሰፊ ጉዳት እያደረሰ ነው። በዚህም በአካባቢው አገራት የሰብል ምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚሰራው ስራ ላይ ስጋት መደቀኑን ዓለምአቀፉ ድርጅት አስታውቋል። የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በአህጉሪቷ የተጋረጠውን ይህን ችግር ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የአካባቢው አገራት የኢጋድ ተወካዮች አቅማቸውን አሰባስበው ችግሩን መከላከል እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል። የምስራቅ አፍሪካ አገራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት የሚገጥማችውን ችግር አስቀድመው በመከላከል ላይ ትኩረት አድርገው መስራት አለባቸውም ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም