አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ የመከላከያ ምስክር አሰሙ

122
ኢዜአ፤ጥር 5/2012 በጥረት ኮርፖሬት በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ በተከሰሱባቸው ክሶች የመከላከያ ምስክር አቀረቡ። ተከሳሾቹ የመከላከያ ምስክራቸውን ሲያሰሙ የዋሉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትናንት ለዛሬ በተሰጠው ቀጠሮ መሰረት በዋለው ችሎት ነው። በትናንትናው የችሎት ውሎ በቀረቡባቸው አራት ክሶች ዙሪያ እራሳቸው ማብራሪያ ሲሰጡ የዋሉ ሲሆን በዛሬው እለትም በክሱ ዙሪያ ያብራራሉ ያሏቸውን አራት ምስክሮችን አቅርበዋል። ከቀረቡት ምስክሮች መካከልም ከሰዓት በፊት በነበረው ችሎት ከጁቤንቱስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር በተካሄደ ሽርክና ዙሪያ የባለሙያ የመከላከያ ምስክር አሰምተዋል። ከሰዓት በኋላ በቀጠለው ችሎትም ዱየት ባሳይ የተባለ ኩባንያ ከዳሽን ቢራ ፋብሪካ ጋር በተካሄደው ሽርክና ዙሪያ የኦዲት ባለሙያ የመከላከያ ምስክረነታቸውን ሲሰጡ ውለዋል። ለቀረቡት የመከላከያ ምስክሮችም ግልጽነት ይጎድላቸዋል ለተባሉ ጉዳዮች ከሳሽ አቃቤ ህግ መስቀለኛ ጥያቄ አቅርቦ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተደርጓል። ችሎቱ የቀረቡትን ምስክሮች ካዳመጠ በኋላም ቀሪ የመከላከያ ምስክሮችን ለማድመጥ ለነገ ማለትም ለጥር 6/2012 ቀጠሮ ሰጥቷል። በጥረት ኮርፖሬት የሙስና ወንጀል የተከሰሱት አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ ታደሰ ካሳና አቶ ዳንኤል ግዛው በትናንትናው የችሎት ውሏቸውም መጥሪያ ደርሷቸው ያልቀረቡ ምስክሮች እንዲቀርቡላቸው ተጨማሪ ትዕዛዝ እንዲሰጥ የተከሳሽ ጠበቃ መጠየቃቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም