በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ምክንያት በየሁለት ሰዓቱ አንድ ሰው ለህልፈተ ህይወት ይዳረጋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ምክንያት በየሁለት ሰዓቱ አንድ ሰው ለህልፈተ ህይወት ይዳረጋል

ኢዜአ፤ጥር 5/2012 በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ምክንያት በየሁለት ሰዓቱ አንድ ሰው ለህልፈተ ህይወት እንደሚዳረግ አንድ የዘርፉ ጥናት አመላከተ። በጥናቱ በቀን 13 ሰዎች በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸው እንደሚቀጠፍም ተመልክቷል። በኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነት አፈጻጸም ግምገማ ላይ ያተኮረ ውይይት በትራንስፖርት ሚኒስቴር እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስተባባሪነት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ዛሬ ተካሂዷል። በመድረኩ በቀረበ የመንገድ ደህንነት ላይ ያተኮረ አንድ ጥናት እንዳመላከተው በትራፊክ አደጋ ምክንያት በየሁለት ሰዓቱ አንድ ሰው ለሞት እንደሚዳረግ አመላክቷል። እ.አ.አ. ከ2016 እስከ 2018 ባለው ጊዜ ውስጥ 4 ሺህ 732 ሰዎች ለሞት የተዳረጉ ሲሆን ይህም በአማካኝ በቀን 13 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸው እንደሚቀጠፍ ነው ጥናቱ ያመላከተው። ጥናቱ 85 በመቶ የሚሆነው የትራፊክ አደጋ የሚከሰትባቸው አካባቢዎች ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ክልል እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሆናቸውን ለይቷል። 52 በመቶ የሚሆነው የትራፊክ አደጋ የሚደርስው በተሳፋሪዎች ላይ መሆኑን የተመለከተው ጥናቱ 33 በመቶ የሚሆነው አደጋ ደግሞ በእግረኞች ላይ መሆኑን ነው ያሳየው። 60 በመቶ የሚሆነው አደጋ የሚደርሰው ከ18 እስከ 52 የዕድሜ ክልል ውስጥ በሆኑ ሰዎች ላይ ነው። በኢትዮጵያ የአስፓልት መንገድ ሽፋን 14 በመቶ ቢሆንም 79 በመቶ የሚሆነው የትራፊክ አደጋ የሚደርሰው እዚሁ አስፓልት መንገድ ላይ ነው። የጥናቱ አቅራቢ ዶክተር ጌቱ ሰገኔ የትራፊክ አደጋ የሚደርሰው የመሰረተ ልማት ዲዛይን ለብዙሃን ትራንስፖርትና ለሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች ምቹ ባለመሆኑ እንደሆነ ጠቁመዋል። የአሽከርካሪዎችና መንገደኞች ግንዛቤ ማነስ፣ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ደካማ መሆን፣ ያረጁ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መበራከት፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ክፍተትና የቁጥጥር ስርዓቱ ደካማ መሆን የችግሩ መንስኤዎች እንደሆኑ ገልጸዋል። በትራንስፖርት ሚኒስቴር የመንገድ ትራንስፖርት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ፈትያ ደድገባ በበኩላቸው የብዙ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን የመንገድ ደህንነት አደጋ ለመቀነስ ከህብረተሰቡ ጋር በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚሰራ ተናግረዋል። የጥናቱ ውጤት መነሻነት በዘርፉ እየተከናወነ ላለው ስራ አስፈላጊ ግብዓቶችን እንደሚያስገኝ እና በዚህ ውጤት ለማምጣት እንደሚሰራ ጠቁመዋል። ከቅርብ አመታት ወዲህ የትራፊክ አደጋ በኢትዮጵያ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ይታወቃል።