ለውጥን በመደገፍ አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት እንቃወማለን...የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች

50
ደሰኔ 17/2010 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ በወጡ ንጹኃን ላይ የደረሰውን የቦንብ ጥቃት እንደሚያወግዙ በደቡብ ወሎ ዞን የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡ የተጀመረውን ሀገራዊ አንድነትና ሰላም ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ነሪዎቹ ዛሬ ባደረጉት የድጋፍ ሰልፍ አረጋግጠዋል፡፡ በሰልፉ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኮምቦልቻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ካህን አባ ሞገስ ሲሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ መድረኮች የሚያስተላልፏቸው መልእክቶች በእምነቱም ዘንድ የሚደገፉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ልዩነትን አስወግደን አንድነትን እናረጋግጥ፣ ባልተረጋገጠ ያለፈ ታሪክ ተጠላልፈን ጥላቻንና በቀልን ለትውልዱ ከምናወርስ በይቅርታ ወደ አዲስ ምእራፍ እንሸጋገር” የሚል መሪን ለማድነቅ በተሰበሰበቡ ንጹሃን ላይ ጥቃት መፈጸም የሰይጣን ተግባር ነው ብለውታል። የኃይማኖት አባቶችም የተጀመረው አንድነት እንዳይቀለበስ በጸሎትና ህዝቡን በማስተማር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈው በሞት ለተለዩት ቤተሰቦች መጽናናትን፣ ጉዳት ለደረሰባቸውም በፍጥነት ማገገምን ተመኝተዋል፡፡ በኮምቦልቻ ቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ አደም አሚኑ ከ15 ዓመታት በላይ በአረብ አገራት በስደት መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ በሀገራቸው ሰርቶ የመበልጸግ፣ ተናግሮ የመደመጥ እድል በማጣታቸው ስደትን መርጠው እንደነበር አስታውሰው፤ በስደት ላይ ሳሉም ለእስራትና እንግልት መዳረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ አሁን የተጀመረው የአንድነት መንፈስ ዜጎች በአገራቸው ሰርተው እንዲበለጽጉ የሚያደርግ በመሆኑ ለውጡን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡ የድጋፍ ሰልፉ አስተባበሪ አቶ ዳዊት ታደሰ በበኩላቸው “ኢትዮጵያ አኩሪ ታሪኳን ጠብቃ ያቆየችው ልዩነት ስሌለ ሳይሆን በልዩነት ውስጥ ተከባብሮ የመኖር የዳበረ ባህል ስለነበራት ነው” ብለዋል፡፡ “ይህ አኩሪ ባህል እየተሸረሸረ መጥቶ አገሪቱ ወደ አላስፈላጊ አደጋ እየገባች ነበር” ያሉት አስተባባሪው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሯቸው የለውጥ፣ የአንድነትና የይቅርታ መልእክቶች ተለያይተው የነበሩ ወንድማማች ህዝቦችን በፍቅር እያስተሳሰረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “በአንድነትና በፍቅር፣ በይቅርታና በህግ የበላይነት ከምንም በላይ ተጠቃሚዎቹ እኛ ነን” ያሉት አቶ ዳዊት ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅማቸውን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ለውጦች እንዳይቀለበሱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡ በድጋፍ ሰልፉ 30 ሺህ የሚገመት የኮምቦልቻና የአካባቢው ነዋሪ በኮምቦልቻ ኳስ ሜዳ የተሰባሰበ ሲሆን በአሮጌ አስተሳሰብ አዲሱን ትውልድ መምራት አይቻልም፣ ሙስና ተቆርጦ መጣል ያለበት ካንሰር ነው የሚሉና ሌሎች መልእክቶችን ያያዘ መፈክር በሰልፉ ተደምጧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም