ክልሎች የአዕምሯዊ ንብረት አገልግሎት በመስጠት ፈጠራን ማሳደግ የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ

118
ኢዜአ፤ጥር 5/2012 ክልሎች ለፈጠራ ስራዎቻቸው የአዕምሯዊ ንብረት አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ማሳደግ የሚያስችላቸውን መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ስለሰነዱ ለየክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊዎች ግንዛቤ የሰጣቸው ሲሆን ሰነዱ ስለሚያስቀምጣቸው ኃላፊነቶች፣ የትብብርና የድጋፍ ወሰኖች አወያይቷል። ስምምነቱ ጽህፈት ቤቱ የተሰጠውን ተቋማዊ አገልግሎቶችን ባልተማከለ አሰራር ለሁሉም የፈጠራ ባለቤቶች  በየክልሉ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተደራሽ እንዲያደርጉ ውክልና የሚሰጥ ነው ተብሏል። የጽህፈት ቤቱ ዋናዳይሬክተር ኤርሚያስ የማነ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የባለድርሻ አካላቱና የአዕምሯዊ ንብረት አገልግሎት ስራዎች ተያያዥነት ስላለው ስምምነቱ ለአገሪቷ የፈጠራ ባለቤቶች ዕውቅና ከመስጠቱም በላይ ፈጠራን ያበረታታል፣ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ያግዛል። ፈጠራ ለታዳጊ አገሮች አማራጭ የሌለው የአገር ሀብት በመሆኑም ጥበቃ እንዲያደርጉና ባለቤቶቹም የፈጠራ ስራቸውን በማውጣትና በማስመዝገብ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለባቸው አቶ ኤርሚያስ ለክልሎቹ አሳስበዋል። የተፈረመው ሰነድ አገልግሎቱ ከዚህ በፊት በሀዋሳ፣ በጅማና በባህር ዳር ተወስኖ የነበረውን የአዕምሯዊ ንብረት አገልግሎቱን ውስንነት በማስቀረት በመላ አገሪቷ ለማዳረስ አጋጣሚ ይፈጥራል። ይህም የተቋማቱን ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር ለደንበኞች በቀላሉ ተደራሽ ማድረግንና የጋራ ሀላፊነትን በጋራ በመወጣት ወጪን መቆጠብን ያለመ ነው። ስለሆነም ክልሎቹ ከዚህ በኋላ የተፈራረሙትን መሰረት አድርገው የምክር አገልግሎት፣ የንግድ ምልክትና የፓተንት ምዝገባን እንዲሁም የቴክኖሎጂ ፈጠራና ድጋፍ ማዕከላት ለሆኑት ለየክልሎቻቸው ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አገልግሎቱን ይሰጣሉ። ስምምነቱ ተቋማቱ እንደየክልሎቻቸው ነባራዊ ሁኔታዎችን መሰረት አድርገው ወደፊት የአዕምሯዊ ንብረት  ፖሊሲ እንዲኖራቸው ያስችላቸዋልም ብለዋል አቶ ኤርሚያስ። እንዲሁም ማስፈጸሚያ ዕቅዶችን ማዘጋጀት፣ የሰው ሃይል ማልማትና ለፈጠራ ስራዎች የመጨረሻ ሰርተፊኬት መስጠት ከጽህፈት ቤቱ የሚጠበቁ መሆናቸው ተብራርቷል። የክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊዎችም በበኩላቸው ግንኙነቱ ተቋማዊ እንዲሆንና ቀጣይነት እንዲኖረው ጥያቄ የቀረበ ሲሆን በስምምነቱ አስገዳጅ የሆኑ ጉዳዮች መቀመጥ እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከኦሮሚያ ክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ዶክተር ታሲሳ ክበበው እንዳነሱት ከክልሉ ስፋት አንጻር አሁን ያለው አደረጃጀት የማህበረሰቡ የዕውቀት ሀብቶችን ተደራሽነት ያስቸግራል። ከአማራ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ዶክተር ሰብስበው አጥቃው በበኩላቸው፤ ስምምነቱን አስመልክቶ ለተጠያቂነቱ የድጋፍና የትብብር ስራው ከጽህፈት ቤቱ ጋር በልዩነት መቀመጥ እንዳለበት ጠይቀዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም