በጌዴኦ ዞኑ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ አግኝተናል በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑን አስተዳደሩ ገለጸ

106
ዲላ ሰኔ 17/2010 በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ዜጎች በመንግስት ትኩረት አልተሰጠውም በሚል የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ አግኝተናል በማለት የተሰራጨው መረጃ ትክክል አለመሆኑን የጌዲኦ ዞን አስታወቀ ፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ እንዳሉት በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ ዳግም በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ከኦሮሚያ ክልልና ዞኑን ከሚያዋስኑ አካባቢዎች የተፈናቀሉት በጌዴኦ ዞን ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን በንብረታቸው ላይ ውድመት የደረሰባቸውና የስርቆት ተግባር የተፈጸመባቸው መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉት ዜጎች የአካባቢው ህብረተሰብ፣ የደቡብ ክልልና የፈፌዴራል መንግስት ሰብአዊ ድጋፍ እያደረጉላቸው ቢሆንም ከተፈናቃዮቹ ቁጥር መብዛት ጋር ተያይዞ የሚያገኙት ድጋፍ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት ተፈናቃዮቹ የተጠለሉበት ስፍራ አመቺ አለመሆን ከክረምት ቅዝቃዜ ጋር ተዳምሮ ያሉበትን ሁኔታ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ እነዚህ ወገኖች የደረሰባቸውን ጉዳትና ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ አስመልክቶ መንግስት በቂ ትኩረት አልሰጠም በሚል ሰሞኑን አንዳንድ አካላት የተቃውሞ ሰልፍ እናደርጋለን የሚል አቋም በህዝቡ መካከል እያስወሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ የሚወራው አሉባልታና ከእውነት የራቀ መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው እስካሁንም ሰልፍ ለማድረግ ምንም አይነት ህጋዊ ጥያቄ ለአስተዳደሩ አለመቅረቡን ገልፀዋል፡፡ "ህብረተሰቡ ከአሉባልታዎች ተቆጥቦ የአካባቢውን ሰላም ሊጠብቅ ይገባል" ያሉት አስተዳዳሪው፣ ህጋዊ የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግም የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ተጠብቆ በመንግስት እውቅና መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖችን አስመልክቶ በፌደራል መንግስት ጭምር እንደሚታወቅና ለመፍትሄው ከክልልና ከፌዴራል መንግስታት ጋር በቅርበት እየተሰራበት መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አያይዘው ገልጸዋል፡፡ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደሴ ዳልኬን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በቅርቡ ወደ ስፍራው አቅንተው ተፈናቃዮችን መጎብኘታቸው ይታወሳል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም