የመገናኛ ብዙኅን ባለሙያዎች በሂሳብና ኦዲት ዘገባዎቻቸው ሙያዊ አቅማቸውን ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል ተባለ

107

ኢዜአ  ጥር 4/2012 የመገናኛ ብዙኅን ባለሙያዎች በሂሳብና ኦዲት ዘገባዎቻቸው ሙያዊ አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ።

መገናኛ ብዙሃን በዘርፉ በጋራ ለመስራት የሚያስችል 'የሚዲያ ፎረም' በኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተባባሪነት በትናትናው ዕለት በአዳማ ተመስርቷል።

የኢትዮጵ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ ኦዲት ቦርድ ጋር በመተባበር 'አይ ኤፍ አር ኤስ' ወይም "ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ" ስርዓት ዙሪያ ከአገር አቀፍና የክልል የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በንግድና ግብይት ጋዜጠኝነት መስክ ላለፉት 30 ዓመታት ልምድ ያካበተውና በአሁኑ ወቅት የአዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ታምራት ገብረጊዮርጊስ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በንግድና ግብይት ዘገባዎቻቸው አቅማቸውና ትጋታቸው ውስን እንደሆነ ይናገራል።

ጋዜጠኞች የተቋማት ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ሪፖርትን በጥንቃቄና በጥርጣሬ ለመተንተን ያለባቸው የሙያዊ አቅም ፣ የትጋት ውስንነትና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማዊ አቅም ማነስ ተግዳሮት መሆኑን ገልጿል።

ተቋማት መረጃ የመስጠት ግዴታቸውን አለማክበር ሌላው ተግዳሮት ቢሆንም መረጃ በአንድ ወገን ብቻ በበላይነት ስለማይያዝ የመረጃ ምንጮችን ማፈላለግና መተንተን በባለሙያዎች ትጋት ስለሚወሰን የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸው አመልክቷል።

መገናኛ ብዙሃን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የሚፈጥሯቸው የማስታወቂያ ግንኙነቶች የተነሳ የጥቅም ግጭቶች ወይም ሙያዊ ስነ ምግባር ጉድለት ተዕጽኖ እንደሚፈጥር እምነቱን ገልጿል።

ስለሆነም የተቋማት ግንኙነት ከይዘት ስራዎች መለየት፣ በጋዜጠኞች ስነ ምግባራዊ ደንብ መመራትና ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር መተግበር ተገቢነት እንዳለው አመልክቷል።

መገናኛ ብዙሃን በግልም ሆነ መንግስታዊ ድርጅቶች ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ግድፈት በተመለከተ የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ተመስርቶ የተጠያቂነት ስርዓት አለመኖር ችግር እንደሆነም ጠቁሟል።

ይህም የሚዲያ ተቋማትም ሆነ የጋዜጠኞች በዘርፉ በስፋት እንዲሰሩ የሚያበረታታ እንዳልሆነ ተናግሯል።

ስለሆነም ግድፈት የተገኘባቸው ድርጅቶች ተጠያቂ ማድረግና ማህበረሰቡም በዝምታ እንዳይመለከታቸውና እንዲቃወማቸው ማድረግ ተገቢነት እንዳለው ጋዜጠኛ ታምራት ገልጿል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም ከመድረኩ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ወደፊትም ተቋማትን ከሚቆጣጠረው ከኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ጋር መረጃ ለመለዋወጥና በጋራ ለመስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩም መገናኛ ብዙሃን በዘርፉ በጋራ ለመስራት የሚያስችል 'የሚዲያ ፎረም' በኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተባባሪነት ተመስርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሠይፈ ደርቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሚዲያ ፎረም የመረጃ ክፍተትን ለመሙላትና የባለሙያዎችን የአቅም ውስንነት ለመፍታት ያግዛል።

የሚዲያ ፎረሙ መመስረት ብዙ ባልተሰራበት የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ዘርፍ ተሞክሮና ስልጠናዎችን ለማካሄድ፣ አዳዲስ ሃሳቦችን ለመፍጠር እንደሚጠቅም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ካለው ግንኙነት በተጨማሪ በክልሎች 38 ቅርንጫፍ እንዳሉት ገልጸው፤ የሚዲያ ፎረሙን በክልሎችም ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሂክመት አብደላና አቶ ሠይፈ ደርቤ የፎረሙን መመስረት አብስረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም