በአማራ ክልል የዘንድሮው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ተጀመረ

49
ኢዜአ ጥር 4 /2012...በአማራ ክልል የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ዛሬ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ተጀመረ። ለአንድ ወር በሚቆየውና በወረዳው በተንካቲት ገንዳ ውሃ ቀበሌ በተጀመረው ንቅናቄ ከ7 ሺህ በሚበልጡ ተፋሰሶች ሥራው እንደሚካሄድ ተገልጿል። የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መለስ መኮንን በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት እንደተናገሩት ሥራውን ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕድገት ማጠናቀቂያ ዓመት ጋር በማስተሳሰር በልዩ ትኩረት ይከናወናል። በሥራው 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን አርሶ አደሮች የሚሳተፉባቸው የልማት አደረጃጀቶች መፈጠራቸውን ተናግረዋል። በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በሚተገበረው ሥራ ፣ በዛሬው ዕለትም በሶስት ዞኖችና በ27 ወረዳዎች በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል። በሥራው በሚሰማራው የሰው ኃይል ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው አስታውቀዋል። በክልሉ ባለፉት ዓመታት በ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በተከናወነው ሥራ ውጤት እንደተመዘገበበት አስታውሰዋል። አርሶ አደሩን በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ አደረጃጀቶች ተጠቃሚ ለማድረግ ዓዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኦርጌሳ ናቸው። አርሶ አደሩ ሥራው የሚያገኘውን ጥቅም በመገንዘብ የዘወትር ተግባሩ እንደያደርገው አሳስበዋል። መንግሥት የጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማስቀጠል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ትኩረት ሊሰጥባቸው እንደሚገባም አመልክተዋል። ለዚህም አርሶ አደሩ ክትትልና ድጋፉንን እንዲያጠናክር ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል። በተፈጥሮ ሀብት ልማትና  ጥበቃ ግንባር ቀደም ከሚባሉ ክልሎች አንዱ በመሆን የያዘውን ግንባር ቀደምትነት ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል። ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በእርሻ ማሳቸው ባካሄዱት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ውጤታማ እንደሆኑ የተናገሩት አርሶ አደር ቢሻው ጌትነት፣ በማሳቸው ያከናወኑት የልማትና የጥበቃ ሥራ ምርታማቸው በሶስት እጥፍ እንዳደገ ገልጸዋል። በሥራው በእንስሳት መኖ አቅርቦትና የውሃ አካላትን በማጐልበት ተጠቃሚ አድርጎኛል ብለዋል።በያዝነው ዓመትም የተጠናከረ እንቅስቃሴ በማድረግ ተጨማሪ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚጥሩ ተናግረዋል። በንቅናቄው አጀማመር መርሐ ግብር ላይ የክልሉና የፌዴራል አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም