ለሰልፍ አደባባይ በወጡ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት እናወግዛለን....ከፍተኛ ሴት አመራሮች

99
አዳማ ሰኔ 17/2010 ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ድጋፋቸውን ለመግለጽ አደባባይ በወጡ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት እንደሚያወግዙ በሴቶችና ህፃናት ዘርፍ የሚሰሩ ከፍተኛ ሴት አመራሮች ገለፁ። ድርጊቱ ከማውገዝ ባለፈ ለላቀ ትግል እንደሚያነሳሳቸው የገለፁት የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለም ፀጋይን ጨምሮ የደቡብ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዎች ናቸው። የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ፀጋይ ለኢዜአ እንደገለፁት ለሰላም፣ ለአንድነትና ለፍቅር ያለውን ቁርጠኝነት ለመግለጽ በተሰበሰበ ሰላማዊ ህዝብ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት የፈሪዎችና የተሸናፊዎች ድርጊት ነው። ድርጊቱ የሚወገዝ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ በጥቃቱ ለተጎዱ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል። "በቦምብ ፍንዳታው ተጎድተው በህክምና ላይ የሚገኙት ከሕመማቸው በፍጥነት አገግመው እንዲወጡ ተገቢውን ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል። ከሰላም ዋነኛ ተጠቃሚዎች ሴቶችና ህፃናት የመሆናቸውን ያክል ግንባር ቀደም ተጠቂዎችም ስለሚሆኑ ሴቶች አንድነታቸውን በማጠናከር ማንኛውንም ፀረ ሰላም ድርጊት አጠናክረው እንዲታገሉት ጥሪ አቅርበዋል። የደቡብ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው "የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ ሂደት ለመደገፍና ጅምራቸውን ለማበረታታት በተካሄደው ሰልፍ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈፀም ሰብአዊነት የጎደለው ድርጊት በመሆኑ ሁላችንም እናወግዘዋለን" ብለዋል። በድርጊቱ የተሳተፉ ኃይሎች ለህግ ቀርበው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲፋረዳቸውም ጠይቀዋል ። "የጥፋት ድርጊቱ በየትኛውም መንገድ ተቀባይነት የሌለው ፀያፍና ጭካኔ የተሞላበት በመሆኑ በመላው የክልሉ ሴቶች ስም አምርረን እናወግዘዋለን" ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ የኋላሸት ገብሬ ናቸው። ጠቅላይ  ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳዩት ለውጥና እየታየ ያለው አንፀባራቂ ውጤት የዘርና የጾታ ልዩነት ሳይኖር ድጋፉን ለመስጠት በወጣው ህዝብ ላይ የተፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት እንዳይደገም መንግስት ተገቢ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል። የትግራይ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር የትምወርቅ ገብረመስቀል በበኩላቸው "አሁን እየታየ ያለውን ጥሩ የለውጥ መንፈስ እንደ ትግራይ ክልል ሴቶች እንጋራዋለን" ብለዋል። በትናንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ትኩረት ያደረገና ንፁሃን ዜጎችን ሰለባ ያደረገውን ጥቃት በጥብቅ እንደሚያወግዙት ተናግረዋል፡፡ "እየታየ ያለው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ለውጥ ከተደናቀፈ ግንባር ቀደም ተጠቂዎች እኛው ሴቶችና ህፃናት በመሆናችን ድርጊቱን ከማውገዝ ባሻገር በጽናት ልንታገለው ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል። ከፍተኛ የሴት አመራሮቹ ለሰው ሕይወትና አካል ጉዳት ምክንያት በሆነው ጥቃት ላይ የተሳተፉ ሁሉ ለህግ ቀርበው ተገቢው ቅጣት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም