ለኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን ደህንነት በመንከባከብ የድርሻችንን እንወጣለን…የድሬዳዋና አካባቢው ነዋሪዎች

91

ኢዜአ ጥር 1/2012 የኢትዮ-ጅቡቲ ዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርትን ደህንነት በመጠበቅ አስተማማኝ አገልግሎት እንዲሰጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋና የሽንሌ ነዋሪዎች ተናገሩ። ላለፉት ሁለት ዓመታት አገልግሎት እየሠጠ የሚገኘው የኢትዮ-ጅቡቲ ዘመናዊ ባቡር ደህንነት ቀን በድሬዳዋ ዛሬ ሲከበር ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት የባቡር አገልግሎቱ ለአካባቢው እድገት መፋጠን ቁልፍ ሚና አለው።

የሽንሌ ወረዳ ነዋሪ አዛውንት አቶ መሐመድ አሊ እንደገለጹት የሲቲ ዞን ነዋሪዎች ከመቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ የባቡር ጥቅሞችን በአግባቡ ያጣጣሙ በመሆናቸው አዲሱን መስመር በመንከባከብ የአገልግሎት ዘመኑን ከፍ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው፡፡

ከስርቆትና የጋማ ከብቶች ወደ ባቡር መስመር መግባት ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ የሚገኘውን ችግርም ከሌሎች ጋር በመቀናጀት እንደሚከላከሉ አስረድተዋል።

የድሬዳዋ መልካ ጀብዱ ቀበሌ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብዱላሂ አብዶ በበኩላቸው እንደተናገሩት የባቡር መስመሩ ለድሬዳዋና ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጣል።

በእስከ አሁኑ ድሬዳዋ ከጅቡቲ ጋር ያላትን ቅርበት በመጠቀምና የባቡሩን አገልግሎት መጀመር ተከትሎ በርካታ ባለሃብቶች በመልካ ጀብዱ ቀበሌ ልማትን እያፋጠኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በባቡር ትራንስፖርት ተጠቅመው ጅቡቲ ወደብ በቀላሉ ዕቃ ማጓጓዝ መቻላቸው የድሬዳዋን ቀጣይ ዕድገት ለማፋጠንና የሥራ እጥ ቁጥርን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

በመሆኑም የባቡር ትራንስፖርት ዘርፉን በየደረጃው የሚገኘው ወጣትና ነዋሪ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የራሱን ሃብት እንዲጠብቅ የሚያደርጉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አይሻ ሐሰን በበኩላቸው የባቡር አገልግሎቱ ድሬዳዋን ከጅቡቲ ከማገናኘት ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩንም ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ባቡሩ ወደ አካባቢው የሚመጡ እንግዶችን በማበራከት የንግድ እንቅስቃሴውንም ስለሚያግዝ የነዋሪውን የወደፊት ተስፋ የሚያለመልም እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በቻይና የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ተገንብቶ ላለፉት ሁለት ዓመታት አገልግሎት እየሠጠ የሚገኘው የኢትዮ-ጅቡቲ ዘመናዊ ባቡር የሚፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጥ ያለመና "ለደህንነታችን ባቡራችንን እንውደድ" በሚል መሪ ቃል በተካሔደ አከባበር ላይ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም