በዋልታ ቴሌቪዥን የፌስቡክ ገጽ የተላለፈውን ሀሰተኛ ዜና በተመለከተ በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርምራ ተጀመረ

95
ኢዜአ ጥር 1/2012 የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤልን በተመለከተ በዋልታ ቴሌቪዥን የፌስቡክ ገጽ ከተላለፈው ሀሰተኛ ዜና ጋር በተያያዘ በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርምራ መጀመሩን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት 11 ሰዓት ከ 20 ደቂቃ አካባቢ በዋልታ ቴሌቪዥን የፌስቡክ ገጽ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ባልታወቀ ሁኔታ ሞቱ በሚል የተሳሳተ መረጃ መሰራጨቱ ይታወሳል። ዋልታ ቴሌቪዥንም በፌስቡክ ገጹ ላይ የተላለፈው የሀሰት መረጃ በማንና እንዴት እንደተለቀቀ እንዲጣራለት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥቆማ ሰጥቷል። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በተጠርጣሪዎች ላይ የጀመረውን ምርምራሂደት አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ተሰጥቷል። በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርምራ ቢሮ የተደራጁና ልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርምራ ዳይሬክተር ኮማንደር አበራ ቡሊና እንዳሉት፤ በወንጀሉ የሚያስጠረጥር መረጃ የተገኘባቸው ሰባት የተቋሙ ሰራተኞች ላይ ምርምራ ተጀምሯል። ምርምራ የሚደረግባቸው የዋልታ ቴሌቪዥንን የፌስቡክ ገጽ የይለፍ ቃል የሚጠቀሙ፤ ከድርጊቱ ጋር ቅርበት ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች እውቅና ውጭ ድርጊቱ ሊፈፀም የማይችል መሆኑንና ግለሰቦቹ ሃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ መሆናቸው በድርጊቱ ያስጠረጥራቸዋል ብለዋል። የምርምራ ሂደቱ ተጀመረ እንጂ አላለቀም ያሉት ኮማንደር አበራ፤ ምርምራው ውስብስብ በመሆኑ በቀጣይ በጥልቀት ማየትን ይጠይቃል ብለዋል። አንድ ተጠርጣሪ በስሙ የይለፍ ቃል በመጠቀም መረጃው የተላለፈ መሆኑ በምርምራ ተረጋግጧል፤ ነገር ግን መረጃውን እርሱ ይልቀቀው ወይስ ሌሎች የይለፍ ቃል ያላቸው ወይም በሌላ በሳይበር ተጠልፎ የተለቀቀ የሚለው በዝርዝር የሚታይ እንደሆነም አመልክተዋል። በድርጊቱ የተጠረጠሩት አካላት ተቋሙ ከሰጠው ጥቆማ በተጨማሪ ለድርጊቱ ቅርበት ያላቸውና ተጠርጣሪ ሊያስብላቸው የሚያስችል መረጃ ያገኘንባቸው ናቸው ብለዋል። በእስካሁኑ ምርምራ ማን ምን ሲያደርግ እንደነበረ የሚያመላክቱ ቴክኒካዊ የሆኑ መረጃዎች ስለመገኘታቸውም ጠቁመዋል። በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሳይበር ወንጀልና ሌሎች ውጫዊ ጉዳዮች መኖር ስለአለመኖራቸው ለማጣራት ምርምራው ይቀጥላል ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም