አለመግባባቶችን በሠላም ለመፍታት የውይይት ባህል እንዲዳብር ከኃይማኖት ተቋማት ብዙ እንደሚጠበቅ ተገለጸ

68
ኢዜአ ጥር 1/2012፡- አለመግባባቶችን በሠላማዊ መልኩ ለመፍታት የውይይት ባህል እየዳበረ እንዲሄድ ከኃይማኖት ተቋማት ብዙ እንደሚጠበቅ ተገለጸ፡፡ "ሠላም በኃይማኖት እይታ" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ  የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄዷል። የከተማው  የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ቄሲስ አብነት ማሞ በመድረኩ በሰጡት አስተያየት " ባለችን አንዲት ሃገር የኃይማኖት ተቋማትና አባቶች በጋራ በመሰባሰብ ስለሰላም ሊያስተምሩ ይገባል" ብለዋል። ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች አግባብነት ባለው አካሄድ ምላሽ ሳይሰጣቸው ቢዘገዩ የሠላም ችግር ስለሚሆኑ  ለይቶ በፍጥነት ለመፍታት መመካከር እንደሚገባ አመልክተዋል። የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ ያለው  ጌታቸው በበኩላቸው ልዩነቶችን በሃሳብ የበላይነት የማሸነፍ የውይይት ባህል ማዳበር  ከዘመናዊነትና ከስልጣኔ ማሳያዎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። ህዝቡን የሚያውኩ ፣ በቤተ-ዕምነቶች መካከል አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የአምልኮ ቦታዎች መጠጋጋት፣  ባልተፈቀዱ ስፍራዎች ሰበካ ማድረግና መሰል የስነ-ምግባር ጥሰቶች ሊታረሙ እንደሚገባ አሳስበዋል። አስተዳደሩ በማይታረሙት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ  አስታውቀዋል፡፡ አባ ገብረእግዚአብሄር ገብረማሪያም በሰጡት አስተያየት የሃሳብም ሆነ ሌሎች ልዩነቶችና ግጭቶች ተፈጥሮዊና ከፈጣሪ የተሰጡ ጸጋዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። ይህን ተፈጥሮ የለገሰውን ልዩነት በአግባቡ መያዝና መምራት ለሰው ልጆች የተሰጠ ኃላፊነት እንጂ በረባ ባልረባ  የጥፋት መነሻ ማድረግ ኃይማኖት አለኝ ከሚል እንደማይጠበቅ ገልጸዋል። "ሠላም በኃይማኖት እይታ " በሚል ጽሁፍ ያቀረቡት  ሃጂ ናስር ዩሱፍ በበኩላቸው "ሠላም የቅዱሳት መጻህፍት ዋና ተልዕኮ መሆኑን ኃይማኖት አለኝ የሚል ሁሉ ሊያውቅ ይገባል" ብለዋል፡፡ ሠላምን ለመጠበቅ መወያየትና መመካከር ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው  የኃይማኖት ተቋማት የመልካም ስነ-ምግባር ትምህርት መስጫ ማዕከላት መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል። አለመግባባቶችን  በመተማመን መንፈስ በሰላም ለመፍታት የመጀመሪያው አማራጭ የሆነው የውይይት ባህል እንዲዳብር ከኃይማኖት ተቋማት ብዙ እንደሚጠበቅም ተመልክቷል። በመድረኩ የወላይታ ሶዶ ከተማ  የኃይማኖት ተቋማት መሪዎችና አባቶች እንዲሁም  የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም