የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎችን ማጎልበት እንደሚገባ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ

101
መቀሌ ሰኔ17/2010 የኢትዮጵያ ምሁራን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የጀመሯቸውን የፈጠራ ስራዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢፌዴሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አሳሰበ ። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስራና ውጤትን አስመልክቶ በመቀሌ ከተማ ሰማዕታት ሃውልት አዳራሽ ዛሬ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ተካሒዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው እንደገለጹት በሃገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የተሻለ እድገት እንዲመጣ ምሁራንና ባለሙያዎች የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ለሀገር ልማትና እድገት የሚበጁና ስራን የሚያቀላጥፉ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማፍለቅ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። “ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጪ በአንድ ሃገር ውስጥ ልማትና እድገት እንዲሁም የኢንዱስትሪ መር የልማት ስትራቴጂ ማፋጠን አይታሰብም” ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ዘርፉን ለማሳደግ ያለ  ዕረፍት መስራትና ለውጤት ማብቃት እንደሚገባ ገልጸዋል። በትግራይ በ2010 በጀት ዓመት በሳይንስና ቴክኖሎጂ በአዳዲስ የፈጠራ ስራ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ 95 የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማበረታታት እውቅና መሰጠቱን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አብረሃ ኪሮስ ናቸው። ምሁራኑና የፈጠራ ባለሙያዎቹ ጥቅም ላይ ካዋሏቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከልም በመስመር መዝራት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ፣ ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ቁሳቁሶች፤የጎርፍ መከላከያና የምግብ መስሪያ ዘመናዊ ማሽኖችና ሌሎችንም ጠቅሰዋል። በአውደ-ጥናቱ ከቀርቡ ጥናታዊ ፅሁፎች መካከልም፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ለዘላቂ ልማት፤የእንስሳት ሃብት ልማት ማዘመን፤የከተሞች የአረንጓዴ ልማት ስራዎችና ሌሎችም ላይ ያተኮሩ ጉዳዮች ይገኙባቸዋል። ማምሻውን በሚጠናቀቀው አውደ ጥናት ላይ 300 የሚጠጉ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ምሁራን ፤የፈጠራ ባለመብቶችና ሌሎችም እንግዶች እየተሳተፉ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም