ኢትዮጵያና ጃፓን ጥራቱን የጠበቀ የመሰረተ ልማት ግንባታ ለመከወን ተስማሙ

49

ኢዜአ፤ ጥር 1/2012 ኢትዮጵያና ጃፓን ጥራቱን የጠበቀ የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማከናወን የሚያሰችላቸውን  የትብብር ስምምነትማድረጋቸውን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከፍተኛ ጥራትያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ያተኮረው የኢትዮጵያና ጃፓን 2ኛ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በኮንፍረንሱ ላይ የትራንስፖርትና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴሮች ከጃፓን የመሰረተ ልማት፣ የመሬት፣ የትራንስፖርትና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በአገሪቷ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን የመገንባት እቅዶች መኖራቸውንና ትኩረታቸውም ብዛት ላይ ሳይሆን ጥራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የጃፓን የመሰረተ ልማት ግንባታ የዳበረ ልምድ ለኢትዮጵያ መንግስትና ለግሉ ዘርፍ ተቋማት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ እንደሆነም ገልጸዋል።

ስምምነቱ ጥራቱን የጠበቀ የመሰረተ ልማት ግንባታን ለማከናወን የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ ጥራቱን የጠበቀ የመሰረተ ልማት ግንባታ ለመከወን የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ወሳኝ በመሆኑ ይህንኑ ለማጠናከር እየተሰራ ነው።

ጃፓን በመሰረተ ልማት ግንባታ የኢትዮጵያን ፕሮጀክቶች አስተዳደር አቅም በማጠናከርና በመንገድና ሌሎች ግንባታዎች ላይ በመሳተፍ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷንም አንስተዋል።

ከጃፓን የመንግስትና የግል ተቋማት ጋር እየተካሄደ ያለው ኮንፍረንስ የአገራቱን ትብብር ለማጠናከርና በኢትዮጵያ ጥራቱን የጠበቀ መሰረተ ልማት በመገንባት ረገድ ያሉ ተግዳሮቶችና እድሎችን በተመለከተ ለመወያየት እድል እንደሚፈጥርም ሚኒስትሯ አክለዋል።

የጃፓን የመሰረተ ልማት፣ የመሬት፣ ትራንስፖርትና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሚስተር ኖቡሀይድ ሚኖሪካዋ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ለማሻሻል ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወርና ሌሎች ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እነዚህ ማሻሻያዎችና ለውጦችም የጃፓንና የኢትዮጵያን የመሰረተ ልማት ዘርፍ ትብብር ለማጎልበት እድል እንደሚፈጥሩ ነው የተናገሩት።

የጃፓን ኩባንያዎች በፕሮጀክት አስተዳደር፣ የጥራት ቁጥጥርና የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ሽግግር ላይ ለኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጉልህ እገዛ ማበርከት እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

ሚስተር ኖቡሀይድ እንደተናገሩት እየተካሄደ ያለው ኮንፍረንስ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ በጋራ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ለመፍጠር የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ይጠቅማል።

በጃፓን የመሰረተ ልማት ዘርፍ መሪ የሆኑ 20 ኩባንያዎች በኮንፍረንሱ ለመሳተፍና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በአጋርነት ለመስራት መምጣታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም