በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በግል ጸብ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደ መረጋጋት ተመለሰ

167

 ኢዜአ ጥር 1/2012 በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ትናንት ምሽት በሁለት ተማሪዎች ጸብ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደ መረጋጋት መመለሱን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 44 ተማሪዎች ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑም ተመልክቷል።

የዩኒቨርሲቲው የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አየለ ኦዳቶ እንደገለጹት  ሁለት ተማሪዎች ተጋጭተው  ጉዳዩ በይቅርታ ተፈትቶ ነበር።

ሆኖም ትናንት ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ አንድ ተማሪ  በስለት ተወግቶ   በህንጻ ኮሪደር ላይ  ወድቆ የተገኘው ተማሪ የህክምና እርዳታ ቢደረግለትም ማትረፍ አልተቻለም ብለዋል፡፡

 ከክልሉ ኮማንድ ፖስት ጋር በመቀናጀት የችግሩን መንስኤ ለማጣራት እየተሰራ እንድሚገኝ አመልክተው  እስካሁን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 44 ተማሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲውም ልዩ አጣሪ ኮሚቴ በማዋቀር እያጣራ መሆኑና በጉዳዩ ዙሪያ ከተማሪ መማክርት አባላት ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ቀጥሎም ከተማሪዎች ጋር ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የውጪ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ዳይሬክተር ወይዘሮ አርማዬ አሰፋ በበኩላቸው በወንጀሉ የተሳተፉ አካላት ላይ ተገቢውን ማጣራት ተደርጎ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲው የጸጥታው ችግር በመቀረፉ  የመማር ማስተማር ስራው ሳይተጓጎል መቀጠሉን ገልጸዋል።

በመጪው ሰኞ  የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት የማጠቃለያ ፈተና እንደሚጀመር የተናገሩት ዳይሬክተሯ ተማሪው አሁን ያለው ሰላማዊ ሁኔታ እንዲቀጥል የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም