ማዕከሉ የእንስሳት መኖ እጥረት ለማቃለል የሚያስችል ምርምር እያካሄደ ነው

107

ኢዜአ ታህሳስ 30/2012 የመቀሌ እርሻ ምርምር ማዕከል የእንስሳት መኖ እጥረት ለማቃለል የሚያስችል ምርምር ከአርሶ አደሮች ጋር በመተባበር እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።

ማዕከሉ  በ11 አዳዲስ የመኖ ዝሪያዎች ላይ ምርምር እየተካሄደ ነው።

የምርምር ስራው ለየአካባቢው ስነምህዳር  ተስማሚ ፣ ምርታማነት ፣ የፕሮቲን መጠንና ከአርሶአደሩ አቅም አንፃር የእንስሳት መኖ  ፋይዳ ላይ በማተኮር  ነው በማዕከሉ እየተካሄደ ያለው።

በማዕከሉ የእንስሳት ስነ ምግብ ተመራማሪ አቶ ክብሮም ገብረመስቀል ለኢዜአ እንደተናገሩት የእንስሳት ምርምር እያካሄዱ ያሉት ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ነው።

ምርምሩ እየተካሄደባቸው ካሉት 11  የ "አልፋአልፋ" ዝሪያዎች መካከል በፕሮቲን ይዞታቸውና በሚሰጡት የምርት መጠን ሁለት መመረጣቸውን  ተናግረዋል።

ከተዘራ  በሶስት ሳምንት ውስጥ ለመኖነት የሚደርስና  እርጥበትን ለማከማቸት  የሚያግዝ መገኘቱም ተመልክቷል።

በተጨማሪም ለእንስሳት መኖነት የሚውሉ የሳር ዝርያዎችና ቅጠላቅጠሎች ላይ ምርምር እየተካሄደ መሆኑን ተመራማሪው አስረድተዋል።

እስካሁን በተመረጡ የግጦሽ ቦታዎች በተካሄዱ የምርምር ስራዎች አርሶ አደሩ ከሚጠቀምበት የግጦች ቦታ እስከ ስምንት በመቶ የፕሮቲን ይዘት ጭማሪ መገኘቱም ተጠቅሷል።

በክልሉ  ያለውን የእንስሳት መኖ እጥረት ችግር ለማቃለል አርሶአደሩ በሚጠቀምባቸው የግጦሽ ቦታዎች ያለውን ዝርያ ለማሻሻልም ተጨማሪ የምርምር ስራዎች መቀጠላቸውን ተመራማሪው ገልጸዋል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ሓውዜን ወረዳ ከሚገኙ ተመራማሪ አርሶአደሮች መካከል አቶ ገብረመድህን ገብረስላሴ እንዳሉት ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ የእንስሳት መኖን ለማሻሻል  ከባለሙያዎች ጋር  ምርምር እያካሄዱ ነው።

ሶስት ዓይነት የ"አልፋአልፋ" ዝሪያዎች በማሳቸው በመዝራት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ለወተት ላሞቻቸው የሚያገለግል መኖ በቅርበት ማግኘት እንደቻሉ ጠቅሰዋል።

በዚህም የተሻለ ወተት ምርት እንዳገኙ ገልጸው የመኖ ልማቱን ለማስፋፋትና የተሻለ ዝሪያ ያላቸው የወተት ላሞች ለመግዛት ማቀዳቸውንም ተናግረዋል።

በማሳቸው እየተካሄደ ያለው የእንስሳት መኖ ምርምር ለከብት ማደለብ የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት  የተናገሩት ደግሞ ሌላው የወረዳው ተመራማሪ አርሶ አደር ገብረስላሴ ገብረማሪያም ናቸው።

በአካባቢያቸው  የእንስሳት መኖ እጥረት እንዳለ ጠቁመው ችግሩን ለማቃለል የሚካሄዱት የመኖ ልማት  ሌሎች  አርሶአደሮችም እንደጠቀሙበት ልምዳቸውን ለማካፈል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም