በኦሮሚያ ምዕራብ ጉጂና በደቡብ ክልል በጌዲኦ ዞኖች አዋሳኝ ስፍራ የተፈጠረውን ችግር እናስተካክላለን....የሁለቱ ዞኖች አስተዳዳሪዎች

97
ዲላ ሰኔ 17/2010 በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለማርገብና ለተፈናቀሉ ዜጎች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የጋራ አቋም መያዛቸውን የሁለቱ ዞን አስተዳዳሪዎች ገለፁ። የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ እንደገለፁት በሁለቱ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ ዳግም በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት 642 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ወደ ጌዴኦ ዞን ተፈናቅለዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም እንዳስረዱት ችግሩ በሁለቱም ወገን የታየ ስለሆነ ለማስቆምና ለዜጎች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የኦሮሚያና ደቡብ ክልል አመራሮች ትናንት በዲላ በጋራ መክረዋል፡፡ በምክክር መድረኩ ከዚህ በፊት ተከስቶ የነበረው ችግር በዕርቅ ተጠናቆ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው መመለስ ጀምረው እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ የተሰሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሥራዎች በቂ ውጤት ሊያመጡ ባለመቻላቸውና የህግ የበላይነትን የማስከበሩ ተግባር በተገቢው አለመፈሙን ገልጸዋል፡፡ ለዜጎች ሕይወት መጥፋት፤ ለንብረት መውደምና መፈናቀል መሪ ተዋንያን የሆኑ አካላትን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ በሚፈለገው ደረጃ ባለመሰራቱ ችግሩ ዳግም ሊከሰት መቻሉ ተገምግሟል፡፡ ከግመገማው በኋላ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለማርገብና ለተፈናቀሉ ዜጎች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በአራት ነጥቦች ለይ የጋራ አቋም መያዙንም ገልጽዋል። አሁንም አዋሳኝ አከባቢዎች ላይ አላፎ አልፎ በሚስተዋሉ ትንኮሳዎች የዜጎች ሕይወት እየጠፋ፤ ቤትና ንብረትም እየወደመ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑ ይህንን በማያዳግም ሁኔታ ማስቆም ያልቻሉ የወረዳና የቀበሌ አመራር አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የጋራ የአሰራር ሥርዐት ተዘርግቷል። በሁለቱም ዞኖች ተጠልለው የሚገኙ የተፈናቀሉ ዜጎች በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግም በሁለቱም በኩል ከክልልና ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት በተደራጀ መልኩ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡ በ"ጎንዶሮ" ባህላዊ የዕርቅ ሥርዐት ችግሩ ዕልባት አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ዳግም በመፈጠሩ የጌዴኦና የጉጂ አባገዳዎች በጉዳዩ ላይ በጥልቀት እንዲወያዩ እንደሚደረግ አስረድተዋል። በኦሮሚያ ምዕራብ ጉጂ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ በበኩላቸው በፀጥታው ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ 178 ሺህ ዜጎች በዞኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ “ባደረግነው የጋራ የምክክር መድረክ ለሰው ሕይወት መጥፋት፤ መፈናቀልና ንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ተግባብተናል” ብለዋል፡፡ በምዕራብ ጉጂ ዞን በኩል በዞን ደረጃ የሚንቀሳቀስ መርማሪ ቡደን ተቋቁሞ እስካሁን 59 ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልፀዋል፡፡ ከህዝብ ጥቆማና ከግምገማ ውጤት በመነሳት እጃቸው አለበት የተባሉ ሶስት የወረዳ አመራር አካላት አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቁመው በሕግ የሚጠየቁበት አግባብም በባለሙያዎች እንደሚወሰን አስረድተዋል። በመድረኩ መግባባት ላይ የደረሱባቸው ጉዳዮች ተግባራዊ እንዲሆኑና ዜጎች ዘላቂ ሰላም እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰሩም አክለው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም