ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት አስተጓጉለዋል ባላቸው ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ

123
ታህሳስ 27/2012 የመማር ማስተማር ሂደትን አስተጓጉለዋል ባላቸው 18 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡ የተማሪዎችን የመሠረተ- ልማት ጥያቄዎች በማሟላት የተቋረጠው ትምህርት በቅርቡ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡ የዩኒቨርሲቲው  አለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጋንፉሬ እንደገለጹት  የተቋሙ  ሴኔት ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በዩኒቨርሲቲው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው ባላቸው 18 ተማሪዎች ላይ  እርምጃ እንዲወሰድባቸው   ውሳኔ    አሳልፎአል፡፡ ውሳኔ ከተላለፈባቸው ተማሪዎች ሁለቱ ሙሉ በሙሉ ከትምህርታቸው እንዲሰናበቱ ነው፡፡ ሰባት ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሶስት ዓመት ፣ ስምንቱ ደግሞ ለሁለት ዓመት ከትምህርታቸው እንዲታገዱ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ተባርሮ የነበረ  አንድ ተማሪ ተመልሶ በተፈጠረው ችግር ውስጥ ተሣትፎ በመገኘቱ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ክስ እንደተመሰረተበት አቶ ደቻሳ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 69 ተማሪዎች የፈጠሩት የዲሲፕሊን ችግር ተጣርቶ በሂደት እንደ ጥፋታቸው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ሴኔቱ መወሰኑንም አመልክተዋል፡፡ በተጓዳኝም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር በተለያየ መልኩ ተሳታፊ በነበሩ ዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ላይ እንደየ ጥፋታቸው መጠን እርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ እንደ አቶ ደቻሳ ገለፃ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ በተማሪዎች ለሚነሱ የኤሌክትሪክ፣  ውሃና የሌሎች  አገልግሎቶችን ክፍተት የማስተካከል ስራ  እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቅርብ ጊዜ ውስጥ የመማር ማስተማር ሥራውን እንደሚጀምርም ጠቁመዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም