በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ካልተረጋገጠ የኢትዮጵያውያን ህልውና የማስጠበቅ ስራ ሙሉ ሊሆን አይችልም ተባለ

3682

ኢዜአ ታህሳስ 27/2012  በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ካልተረጋገጠ የኢትዮጵያውያንን ህልውና የማስጠበቅ ስራ ሙሉ ሊሆን እንደማይችል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።

አገራዊ የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ የሁሉንም ተቋማት እና የሕብረተሰብ ክፍሎች ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚጠይቅም ተመልክቷል።
የሳይበር ደህንነት መረጃን፣ የመረጃ መሰረተ ልማትንና ሌሎች ከሳይበር ጋር የሚተሳሰሩ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም ስዎችን አሉታዊ ተጽዕኖ ከሚፈጥሩ ሳይበር ጥቃቶች መጠበቅ ላይ የሚያተኩር የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ነው።

የመረጃ እና መሰረተ ልማትን ምስጢራዊነት፣ ተአማኒነትን እና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ዋነኛው ተግባሮቹ ናቸው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ኤፍራህ አሊ ስልጠናው ሲጠናቀቅ  እንዳሉት የአንድ ሃገር የህልውና ማረጋገጫ እንደሆኑ የምናውቃቸው ዳር ድንበርን ማስከበር እና የባህርም ሆነ የአየር ክልልን የማስጠበቅ ስራ እንደሚከናወኑ አንስተዋል።

የሳይበር ደህንነት ምህዳር ካልተረጋገጠ ግን እነዚህ ተግባራት ብቻቸውን የአገር ህልውናን ማስጠበቅ አይችሉም ሲሉ ገልጸዋል።

አገራዊ የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ ስራ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው አይደለም፤ ስራው የሁሉንም ተቋማት ቅንጅት ይጠይቃልም ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ  በበኩላቸው የሳይበር ደህንነት ጉዳይ እንደ አንድ የሉዓላዊነት መገለጫ ተወስዶ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሳይበር ደህንነት ዋነኛው ክፍተት የሕብረተሰቡ ንቃተ ሕሊና ዝቅተኛ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት ናቸው።

በዚህም ረገድ የግለሰቦችን ብሎም የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና በማሳደግ በኩል መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የምክር ቤቱ ውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አስካል መኮንን ኤጀንሲው የግለሰቦችን ብሎም የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሆኖም ይህ የግንዛቤ ማስጨበጭ ሥራ በስፋትና ሁሉንም ተደራሽ በሚያደርግ መልኩ መቀጠል እንደሚገባው በማሳሰብ።

በአሁኑ ጊዜ ሳይበር በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ ከዋና ዋና የወንጀል መፈጸሚያ ስልቶች አንዱ በሆነበት ወቅት ችግሩን የሚመጥን ዝግጅት ማድረግ ይገባል ተብሏል።

በዚህ ረገድ በተለይ የሳይበር ደህንነትን የሚመጥን እይታና የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ በስልጠናው ወቅት ተገልጿል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሳይበር ደህንነት ሳምንት በማዘጋጀት በርካታ ተቋማትን ተደራሽ ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ማከናወኑ የሚታወስ ነው።

በቀጣይም የተለያዩ የሥልጠና መርሃ ግብሮችን በመቅረጽ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ግንባታ ሥራው አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኤጀንሲው አስታውቋል።