ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ ባህልን ጠብቀው እውቀትን ለማጎልበት መትጋት አለባቸው— ዶ/ር ፍሬው ተገኘ

413

ኢዜአ ታህሳስ 27/2012  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ ባህልና ወግን ጠብቀው እውቀትና ምርምርን ለማጎልበት መትጋት እንዳለባቸው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ አሳሰቡ።
ዩኒቨርሲቲው “ባህርዳር እንደ ቤቴ” በሚል አንደኛ ዓመት የፕሮግራሙን ዓላማ በሚያሳኩ ዝግጅቶች አክብሯል።

በዝግጅቱ ስነስርዓት የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እንዳሉት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት  ተማሪዎች ኢትዮጵያዊነት ባህልና ወግ መገለጫ ናቸው።

የተለያየ  ቋንቋ፣ ባህልና እሴት ባለቤት የሆኑ ተማሪዎች ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መጥተው በአንድ ቦታ የሚማሩበትና የሚመራመሩበት መሆኑን አመላክተዋል።

አንዱ የሌላውን  ባህልና እሴት ከማስተላፍ ይልቅ የእውቀት ምንጭ የሆነውን የከፍተኛ ምህርት ተቋም የጸጥታ ችግር  መነሻ ቦታ መሆን እንደማይገባ ተናግረዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በማስተሳሰር ዓመት በዓልን አብረው እንዲያሳልፉ እየሰራ እንደሚገኝ ዶክተር ፍሬው ገልጸዋል።

ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ ባህልና ወግን ጠብቀው እውቀትና ምርምርን ለማጎልበት መትጋት እንዳለባቸው  አሳስበዋል።

በዩንቨርሲቲው  የፕሮግራሙ አስተባባሪ ዶክተር ቃለወንጌል ምናለ በበኩላቸው “የባህርዳር እንደቤቴ ” ፕሮግራም የተጀመረው ባለፈው ዓመት እንደሆነ አውስተዋል።

ዓላማውም ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎችን ባህርዳር ከሚገኙ ቤተሰቦች ጋር በማገናኘት ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ነው።

“ይህም ተማሪዎች በበዓል  አብረው እንዲያሳልፉ፣ በማድረግ  ችግር ሲያጋጥማቸው እንዲረዳዱና አካባቢውን በአግባቡ እንዲገነዘቡ የሚያስችል ነው “ብለዋል።

የሶስተኛ ዓመት የባይሎጅ ተማሪው  ሬድዋን ሰይድ በሰጠው አስተያየት” ባለፈው ዓመት የቤተሰብ ትስስር ተፈጥሮላቸው   በዓሉ አብረው እያሳለፉ መቆየታቸውን ተናግሯል።

“ፕሮግራሙ እኛን ከቤተሰብ ጋር ከማስተሳሰሩ ባሻገር በአንድ ቤተሰብ የሚመደቡ ተማሪዎች ልክ እንደ ወንድም እህት እንዲተያዩ በማድረጉ ጠቀሜታው የጎላ ሆኖ አግኝቸዋለሁ “ብሏል።

ተማሪ አጁሉ ኬሎ በበኩሉ”  የባህርዳር ህዝብ በፍቅር፣ በመዋደድና በመተሳሰብ የሚኖር መሆኑን ለበዓል ከምሄድበት ቤተሰቤ መረዳት ችያለሁ “ብሏል።

ትናንት ምሽት በተካሄደው ፕሮግራምም 17 ቤተሰቦች በራሳቸው ፈቃድ ዩኒቨርሲቲውን ጠይቀው የተመደበላቸውን ተማሪዎች በገና በዓል አብረው ለማሳለፍና በቀጣይም እንደ ቤተሰብ ለመተጋገዝ ተረክበዋል።