የኦሮሚያ ክልል የካቢኔ አባላት በሰልፉ ላይ የተከሰተውን አደጋ አወገዙ

61
አዲስ አበባ ሰኔ 17/2010 ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተጠራው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተከሰተው አደጋ የሚወገዝና የህዝቡን አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የካቢኔ አባላት ተናገሩ። የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ጽህፈት ቤት ኃላፊን ጨምሮ የክልሉ ሹሞች ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተገኝተው ከጎበኙ በኋላ ደም ለግሰዋል። የካቢኔ አባላቱ ድርጊቱ ለማንም የማይበጅና የሚወገዝ በመሆኑ ህዝቦች አሁንም የበለጠ ለአንድነታቸው እንዲተጉ የሚያደርግ ነው ብለዋል። የኦህዴድ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንዳሉት ህዝቦች እንተሳሰብ፣ እንፋቀር ባሉበት ቀን ይህ ችግር መፈጠሩ ያሳዝናል። ክስተቱ የበለጠ የኢትዮጵያን ህዝቦችን ፍቅር፣ አንድነትና ሰላም የሚያጠናከር መሆኑን መረዳት ይቻላል ነው ያሉት። የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሃሰንም እንዲሁ ምንም እንኳን አሳዛኝና ያልተጠበቅ ክስተት ቢያጋጥምም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሳይሆን ለበለጥ ውጤት የሚያተጋ ነው ብለዋል። ''ይህ እኩይ ተግባር የአገር አንድነትና ፍቅር የማይዋጥላቸው ኃይሎች ያደረጉት ቢሆንም የበለጠ የሚያቀራርበን ይሆናል'' ያሉት ደግሞ የክልሉ የኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ናቸው። ዶክተር ነገሪ በቀጣይም ይህ ድርጊት ለሰላም፣ ለልማትና ለፍቅር የሚደረገውን እንቅስቃሴ ወደኋላ ሊመልሰው አይችልም ብለዋል። የክልሉ የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው በበኩላቸው ድርጊቱ ሰይጣናዊ ተግባርና ኢትዮጵያዊ ባህሪ የሌላቸው ሰዎች የፈጸሙት ነው ይላሉ። የካቢኔ አባላቱ ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝተዋል። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ ትናንት በሆስፒታሉ ካደሩ 14 ተጎጂዎች መካከል የአንዱ ህይወት ሌሊት ያለፈ ሲሆን ይህም የሟቾችን ቁጥር ሁለት አድርሶታል ብለዋል። አሁን ሆስፒታሉ ውስጥ ከሚገኙ ታካሚዎች ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹ በአንጻራዊ ጤንነት ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት። ትናንት በሰልፉ ላይ ከተጎዱት በቁጥር የሚልቁት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የገቡ ሲሆን አብዛኞቹ ህክምና አግኝተው ወደቤታቸው ተመልሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም