መላው ኢትዮጵያዊያን አመፅንና በቀልን በመተው ለአገራቸው ሰላምና መረጋጋት እንዲተጉ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

120

ኢዜአ ፤ ታህሳስ 27/2012 መላው ኢትዮጵያዊያን አመፅንና በቀልን በመተው ለአገራቸው ሰላምና መረጋጋት እንዲተጉ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡

የገና በዓል ሲከበር የተቸገሩትን በማሰብ ሊሆን ይገባል ሲሉም የእምነቱ አባቶች ምእመኑን መክረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ ካርዲናል ብርሃነእየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን ፕሬዚዳንት ቀሲስ ዮናስ ይገዙ ነገ በመላው ኢትዮጵያ የሚከበረውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ በዚሁ መልዕክታቸው እንዳሉት ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን በአግባቡ በመገንዘብ ሰላምን ሊያደፈርሱ ከሚችሉ ተግባራት መታቀብ፣ ብሎም ለሰላም ዘብ መቆም የመላው ዜጋ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብጹወቅዱስ አቡነ ማትያስ "የክርስቶስ ልደት በዓል ምህረትንና ይቅርታን ለሁላችን ማድረጉን በማስተማር የሚከበር በዓል ነው" ብለዋል።

በመሆኑም ሰላም ከሌለ ኃማኖታዊ ስርዓትንም ሆነ ሀይማኖታዊ ትምህርትን ማካሄድ አይቻለም ያሉት ብፁእነታቸው የሰላም መጥፋት ኑሮን በማናጋት ለዚህኛው ዓለም አጠቃላይ ደስታ እንቅፋት በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ግንባታ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

በተለይም ወጣቶች 'እርስ በእርስ መፋቀርን እንጂ ተጣሉ' የሚል ኃይማኖታዊ አስተምህሮ የሌለ መሆኑን መረዳት አለባቸው ያሉት ሊቀ ጳጳሱ ለህገ ወጥ ድርጊት እንዳይተባበሩም ጥሪ አሰተላልፈዋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና በመርዳት ሊያሳልፍ እንደሚገባ በመጠቆም።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ሊቀ ጳጳስ ብጹ ካርዲናል ብርሃነእየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው "ሀገር ያለህዝብ ህዝብም ያለ ሀገር መኖር እንደማይችል አውቀን አገሪቷን ከጥፋትና ከክፋት መንገድ ልንጠብቃት ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

"በህዝቦች መካከል መተማመን እየጠፋ ዛሬ ወንድም በወንድሙ ላይ እጁን ሲዘነዝር እያየን ነው" ያሉት ካርድናል ብርሃነ እየሱስ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ በኃይማኖታቸው አልያም በብሄራቸው ምክንያት እየተፈናቀሉ ነው፤ ከዚህ ባሻገርም የቤተ እምነቶች መቃጣል አሳዛኝ ነው ብለዋል።

ይህ ዓይነቱ አሳዛኝ ክስተት ይወገድ ዘንድ ሁሉም ከምንም በላይ ለሰላምና ይቅር ባይነት እንዲተጋ አሳስበዋል።

"የተቸገሩትን የሚያስብ ሰው ብጹእ ነው፤ በዓሉን ከአቅመ ደካሞች፣ አስታዋሽ ከሌላቸውና ከተቸገሩት ጋር በመሆን በጋራ ማክበር ተገቢ ነው" በማለትም አጽእኖት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን ፕሬዚዳንት ቀሲስ ዮናስ ይገዙ ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ ምእመኑ የገና በዓልን ሲያከብር ለአገሪቱ ሰላም፣ ለህዝቦች አብሮነት፣ፍቅርና መቻቻል በማሰብ መሆን አለበት ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ችግር ውስጥ እያስገባ ያለውን የሰው ህይወት መጥፋት፣ የእምነት ተቋማት መቃጠል፣ የዜጎች መፈናቀልና የተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ማቋረጥ የሚወገዝ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የአገራችን ህዝቦች ከአመፅና ከበቀል እንዲወጡና መንግስትም ከህዝቡ ጋር በቅርበት በመስራት ኃላፊነቱን እንዲተገብር ቀሲስ ዮናስ መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አገርን ለማስተዳደር ፉክክር የሚያደርጉ የፖለቲካ ፖርቲዎችም የአገራቸው ሰላም እንዳይደፈርስ አርቆ በማሰብ ለህዝቡ የሚያስተላልፉትን መልዕክት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በማከናወን የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም አሳስበዋል።

አገሪቱ ዘንድሮ ታካሄደዋለች ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ሆኖ የህዝብን ሰላም በማያደፈርስ መልኩ እንዲካሄድ የሁሉም ኃላፊነት ነውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም