ያለፈው 2019 የፈረንጆቹ ወይንስ የኢትዮጵያዊያን ብርቱዎች 

94

ቀበኔሳ ገቢሳ (ኢዜአ)

ሽልማት አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን አሊያም ተቋም ላደረገው አስተዋፅኦ ወይም ደግሞ በተለያዩ የፉክክር ወይም የውድድር ሁኔታ አሸናፊ ሆኖ ሲገኝ በተወሰነ አካል የሚሰጠው የዕውቅና አይነት ነው። መሸለም በጣም ደስ ይላል። ዕውቅናውአለም አቀፍ ሲሆን ደግሞ  ደስታው እጥፍ ድርብ ነው። ሃገሬ ሰሞኑን ማሳረጊያውን ባደረገው የፈረንጆቹ 2019 በብርቱ ልጆቿ በሽልማት ተንቆጥቁጣ ነበር። የፈረንጆቹ 2019 ኢትዮዽያን በክብር ማማ ላይ አስቀምጧት ማለፉን ብንገልፅ ማጋነን አይሆንም። ከዕውቁ የኖቤል ሽልማት እስከሌሎቹ የሃገራችን ጀግኖች ደምቀውበት፣ አሸብርቀውበት አልፎ ተርፎ ለሌሎች ምሳሌ ሆነውበት አሮጌው የፈረንጆቹ አመት አልፏል። ምንም እንኳን በሽልማቱ ምክንያት የተሰማን የመኩራራት ስሜት ባያልፍም።

አለም አቀፍ ሽልማቶች በተለያዩ ተቋማት በአይነተ ብዙ ዘርፎች ላይ ውጤታማ ለሆኑ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ይበረከታሉ። በአመራር ጥበብ፣ በሂሳብ፣ በስነፅሁፍ፣ በሰላም፣ በሳይንስ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በበጎ አድራጎት፣ በጀግንነት፣ በስፖርት፣ በስነ ጥበብ፣ ወዘተ መስኮች ውጤታማ ለሆኑ አካላት ዕውቅና ይሰጣል። በተጠቀሱትም ሆነ ሌሎች ዘርፎች ላይ በፈረንጆቹ 2019 ላይ የንግስና ቆብ የጫኑ ኢትዮጵያውንን ስምና ገድል ቀጥለን እንመልከት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) - 2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ

በተለያዩ መስኮች ፈር ቀዳጅ ተግባራትን ላከናወኑ ግለሰቦች እና ተቋማት በየዓመቱ የሚበረከተው የኖቤል ሽልማት በዓለማችን ከሚሰጡ ዕውቅናዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በፈረንጆቹ በ2019 ለ100ኛ ጊዜ የተከናወነው ታሪካዊ የኖቤል የሰላም ሽልማት መርሃግብርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ተሸላሚ አድርጓቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለዚህ ሽልማት ያበቃቸው ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በአገራቸው ውስጥ ለውጥ ለማምጣት መውሰድ በጀመሯቸው እርምጃዎችና በተለይ ከኤርትራ ጋር ሠላም ለማውረድ ባደረጉት ጥረት እንደሆነ ተገልጿል። በኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ግንባታ ለተጫወቱት ሚና እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሰላምና እርቅ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋፅኦ እንደሆነ ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ተጠቅሷል።

የኖቤል የሠላም ሽልማት ለ133 ግለሰቦችና ተቋማት የተሰጠ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 106ቱ ግለሰቦች ሲሆኑ 27ቱ ደግሞ ድርጅቶች ናቸው። ከ106ቱ ግለሰቦች ውስጥ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ 100ኛውን የኖቤል የሰላም ሽልማት በማሸነፋቸው የትልቅ ታሪክ ተጋሪ ሆነዋል።  አልፍሬድ ኖቤል እአአ ኅዳር 18/1888 ዓ.ም አብዛኛው ሃብቱን ለኖቤል ሽልማት መርሃግብር እንዲውል ከተናዘዛቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሠላም ሽልማት ሲሆን፤ ሽልማቱም "በመንግሥታት መካከል ወንድማማችነት እንዲሰፍን አብዝተው ወይም የተሻለ ሥራን ላከናወኑ፣ የጦር ሠራዊቶች ቅነሳና ለሠላም መስፋፋት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ይሰጥ" ይላል። በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ታሪካዊውን እና 100ኛው የሰላም ኖቤል ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሽልማት ስነስርአቱ ወቅት ባደረጉት ንግግርም በርካቶችን አስደምመው የሃሴት እንባ አስነብተዋል። በተለይ “በሰላም እንድታድር ከፈለክ ጎረቤትህ ሰላም ይደር” የሚለውን መልዕክት ያብራሩበት መንገድ በአዳራሹም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ በቴሌቪዥን መስኮት የሚከታተላቸውን ታዳሚ በጥሞና እንዲቆይ ያስገደደ ነበር። ”ለእኔ ሰላምን ማምጣት ዛፍን ተክሎ ከማሳደግ ጋር ይመሳሰልብኛል፥ ዛፍን ተክሎ ለማሳደግ ውሃ እና መልካም አፈር እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሰላምን ለማምጣትም ጠንካራ ተነሳሽነት፣ ታጋሽነት እና መልካም ልብን ይፈልጋል።” ከዚህ በላይ ሰላምን ሊያብራራው የሚችል ቋንቋ ብፈልግ አጣሁ። መድረኩ አይረሴ ሆኖ እንዲቀጥል ያደረገ መልዕክትም በኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ በሬት ሬይስ ተላልፏል። “ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ናት ፣ ስለዚህ ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ነን።” የሚለውን የኮሚቴ ሰብሳቢዋ ንግግርን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ በርካታ ማህበራዊ ድረ ገፆች በጊዜው ተቀባብለውታል።

ፍሬወይኒ መብራኅቱ - 2019 CNN ጀግና (CNN Hero of the Year)

የሲ ኤን ኤን ቴሌቪዥን ሰብአዊ እገዛ የሚያደርግ ተግባር ለሚፈፅሙ ግለሰቦች በየአመቱ ዕውቅና ይሰጣል። ከቀናት በፊት በተሰናበተው የፈረንጆቹ አመት መጨረሻ ላይ በዚህ ዘርፍ የቴሌቪዝን ጣቢያው ኢትዮጵያዊቷ ፍሬወይኒ መብርሃቱን ጀግና ብሎ ሸልሟታል።

ፍሬወይኒ መብርሃቱ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ የሚዉሉ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቅያን ለገጠር ሴት ተማሪዎች ለማዳረስ እና በኢትዮጵያ በሴቶች የወር አበባ ላይ ያለው የተሳሳተ አመለካከት ለማረም የሚያግዙ ስራዎችን ላለፉት 13 ዓመታት ስታከናዉን ቆይታለች። ማርያም ሰባ የተሰኘ የሚታጠብ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያን በማምረት ሥራ ላይ አውላለች። በዚህም የ2019 የሲኤንኤን 'ሂሮ ኦፍ ዘ ይር') ሽልማትን አሸንፋለች፤ የአገር ስምና ዝና በአለም መድረክ በመልካም ሁኔታ እንዲጠራ አድርጋለች።

ፍሬወይኒ “የአመቱ የሲ ኤን ኤን ጀግና” ሽልማትን ያሸነፈችው ለመጨረሻው ፍፃሜ የቀረቡትን አስር ግለሰቦች እና ድርጅቶችን በመብለጥ ነው። ፍሬወይኒ ከዛሬ አስራ ሶስት አመት በፊት ዲዛይን አድርጋው ስራ ላይ እንዲውል ያደረገችው ሊታጠብ የሚችል የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ እስካሁን ስምንት መቶ ሺ ገደማ ሴቶችን ተጠቃሚ አድርጓል።

ፍሬወይኒ ሽልማቷን በተቀበለችበት ወቅት «በጣም አመሰግናለሁ! ምን ማለት እንዳለብኝ እንኳ አላዉቅም። በጣም ተደስቻለሁ ፤ «CNN» ይህን ዕዉቅና ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ። እዉቅናዉ በሁሉ ቦታ ላሉ ሴቶች ሁሉ ይሁን ። ክብር ለሴቶች ሁሉ!  ይህ የሽልማት ደስታ ወቅት ለኔ ብቻ ሳይሆን ለወጣት ሴቶች ሁሉ ነዉ። በዓለም በሁሉም ቦታ ይህን  ችግራችንን ወጥተን ተናግረን አናዉቅም። «CNN » ድምፅችን በጥራትና በከፍታ እንዲሰማ ስላደረገ አድናቆቴን እገልጻለሁ። ክብር ለሁላችሁም!» ስትል ተናግራለች።

አቶ ተወልደ ገብረማርያም - 2019 ምርጥ የአየር መንገድ ስራ አስፈፃሚ (CFPA’s Airlines Executive of the Year)

በፈረንጆቹ 2019 መጨረሻ ወር ዴሴምበር በአምስተኛው ቀን ላይ ሴንተር ፎር አቪዬሽን በተባለ አለም አቀፍ ተቋም በማልታ አንድ ትልቅ መርሃ ግብር ተከናውኗል። መርሃግብሩም የአለማችን ምርጡን የአየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚን አስተዋውቋል። አለም አቀፍ የአቪዬሽን ተቋሙም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብርማርያምን የ2019 መርጥ የአየር መንገድ ስራ አስፈፃሚ ሲል ሸልሟቸዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚው ለአቪዬሽን ዘርፉ ላበረከቱት ሰፊ አስተዋፅኦ እና አየር መንገዱን ተመራጭ ለማድረግ ስትራቴጂክ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የሰሩት ስራ ለሽልማት እንዳበቃቸው ተገልጿል። ዋና ስራ አስፈፃሚው ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላም ዕውቅናውን ለሰጣቸው ተቋም እንዲሁም ለስራ ባልደረቦቻቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተያያዘም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተከታታይ ለ3ተኛ ጊዜ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ በአቬዬሽን ዘርፍ ላበረከተው ጉልህ አስተዋፆኦ ሽልማት ተበርክቶለታል። በSkytrax 2019 የአለም አየር መንገዶች ሽልማት ሥነሥርዓት ላይ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ በማለት አየር መንገዱን ሸልሞታል።

ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም - 2019 የሀርቫርድ የሳይካትሪክና ባዮ-ስታቲሰቲክስ ሽልማት (Harvard Award in Psychiatric Epidemiology and Biostatistics) አሸናፊ ሲሆኑ ሽልማቱ ለፕሮፌሰር አታላይ የተሰጠው በኢትዮጵያ እና በአለም አቀፍ ደረጃ በስነ-አዕምሮ መስክ ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ነው፡፡

ይህ የህይወት ዘመን ሽልማት በየዓመቱ በስነ አዕምሮ ኢፒዲሞሎጂ እና እና ባዮሲታቲክስ መስክ ላበረከቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚሰጥ ሽልማት እንደሆነ ይታወቃል። በጤናው ዘርፍ ሌሎች ሽልማቶችን ማግኘት ተችሏል በዚህም ዶክተር አረጋይ ግርማይ - የሰሜን ካሮላይና ሐኪሞች አካዳሚ የዓመቱ ምርጥ የቤተሰብ ሐኪም ሽልማት (North Carolina Academy of Family Physicians Award) ተሸላሚ ሲሆኑ ዶ/ር ዘቢብ የኑስ - ምርጥ የአፍሪካ ተመራማሪን የ‹‹Future Leaders - African Independent Researcher (FLAIR) Fellowship Award›› አሸናፊ መሆን ችለዋል።

ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ - የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር ‹‹የ2019 ምርጥ ሴት›› ሽልማት (IAAF’s 2019 Woman of the Year Award) እና የ2019 Premio International Fair Play Award አሸናፊ ስትሆን የፕሪሞ አለም አቀፍ የፍትሃዊ የጨዋታ ሽልማት በስፖርት  ዘርፍ ታላቅ አሻራ ላሳረፉ ስፖርተኞች የሚሰጥ ሽልማት ሲሆን ስፖርትን በጥሩ ስነምግባር ፣ በኃላፊነት እንዲሁም በፍትሃዊነት እና በሃቅ ለመሩ አካላት የሚሰጥ ነው። በዘርፉ ከኮሎኔል ደራርቱ በተጨማሪ አትሌት ሰለሞን ባረጋ - የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር ‹‹የ2019 ምርጥ ወንድ ወጣት አትሌት›› ሽልማት (IAAF’s 2019 Male Rising Star of the Year Award) አሸናፊ ሆኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ  The Africa Travel 100 Global Personalities Awards winners ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ይፋ ሆኗል። ምክትል ከንቲባውን ለሽልማት ካበቋቸው መካከል አዲስ አበባን ለሆቴል እና ቱሪዝም ምቹ በማድረግ ፤ በሰብዓዊ እገዛ ላይ በስፋት በመንቀሳቀስ፣ የደካማ እናት እና አባቶችን ቤት በማደስ ለከተማዋ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እና ምግብ በማሟላት የመሳሰሉትን በተጨማሪም የአድዋ ፕሮጀክት ግንባታ ጅማሮ ይጠቀሳሉ።

የፍራንኮ-የጀርመን የሰብአዊ መብቶች እና የሕግ ሽልማት የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ 2016 ሲሆን ሽልማቱም በዓለም ዙሪያ ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ጠበቆች እና እውነትን ለማህበረሰቡ ለሚያሳውቁ ጋዜጠኞች የሚሰጥ ሽልማት ነው። ዘንድሮም አቶ አምሃ መኮንን የዚህ ክብር ባለቤት ሆነዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት ኢትዮጵያውያን በተጨማሪም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም-

የDefend Defenders የ2019 የሰብዓዊ መብት ሽልማት ተሸላሚ፤ የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚንስትር አቶ አህመድ ሺዴ በፋይናሺያል አፍሪካ መፅሄት የዓመቱ ምርጥ የፋይናንስ ሚኒስትር በመባል፣ ማርታ ገበየሁ-የ2019 ዓለም አቀፍ የውሃ ሽልማት (University of Oklahoma International Water Prize)፣ዶ/ር  ሐረገወይን አሰፋ - የ2019 የኬሚስትሪ ጀግና በመባል፣ ዶ/ር ይሁን ድሌ እና ዶ/ር አብዩ ወርቅሉል - የ2019 የዓለም አቀፍ የምግብና እርሻ ልማት ቦርድ ሽልማት (BIFAD Awards for Scientific Excellence) በማሸነፍ የአገራችንን ስም ከፍ ካለ የክብር ማማ ላይ እንዲቀመጥ አድርገዋል።

አርቲስት አብርሃም በላይነህ በ AFRIMA ውድድር የዘንድሮ ዓመት በአፍሪካ ምርጥ የባህላዊ ሙዚቃ ውድድር ዘርፋ #እቴ አባይ በሚለው ስራው አሸናፊ ሆኗል!! በዚህ አመት በተመሳሳይ  እ.ኤ.አ በ2019 በአፍሪካ የባህል ሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ ወደ ናይጄሪያ ሌጎስ ያቀናው የደቡብ ክልል የሙዚቃኞች ማህበር የአመቱ ምርጥ የባህል ቡድን በመሆን በመርሃ ግብሩ ላይ የእውቅና ሽልማት ተሰቶታል። በተያያዘም አርቲስት መላኩ በላይ በባህል የኪነ ጥበብ ዘርፍ ላበረከተው አስተዋፅኦ በሞሮኮ ራባት ከተማ በተካሄደው ቪዛ ፎር ሚውዚክ ፌስቲቫል ላይ ሽልማቱን ወስዷል።

የፈረንጆቹ 2019 ለሃገራችን የየዘርፉ ምርጦች አለም አቀፍ ዕውቅናን ከተከበረ ሽልማት ጋር አጎናፅፏቸው አልፏል። የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ኢትዮጵያ በቀጣዩ የፈረንጆች አመት 2020 በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በቴክኖሎጂ መስክ የተሻሉ እድገቶችን እንደምታስመዘግብ ያላትን ተስፋ በፊት ገፆቻቸው ላይ አስነብበዋል። በሚታይ ተግባራቸው ያደመቋት ልጆቿን ስኬት ለተመለከተ የኢትዮጵያን መፃሂ ብሩህ ትንቢት ከወዲሁ ለመናገር ነብይነት አይጠይቅም። አበቃሁ!!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም