የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ያስገነባውን የመድሃኒት ማቀዝቀዣ ሰንሰለት መጋዝን አስመረቀ

147
ኢዜአ ታህሳስ 25 / 2012 የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የመድሃኒት ማቀዝቀዣ ሰንሰለት መጋዝን ገንብቶ አስመረቀ:: የመድሃኒት ማቀዝቀዣ ሰንሰለቱ ለፖሊዮ ክትባትና ለካንሰር የሚሆኑ መድሃኒቶችን ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ የማቆየት አቅም እንዳለውም ተገልጿል። የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ዋና ዋና የጤና ችግሮች ላይ ያተኮሩ መሰረታዊ መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን በመላ ሃገሪቷ ለሚገኙ ጤና ተቋማት የማቅረብ ስራን ይሰራል። በመሆኑም ኤጀንሲው የሚያቀርባቸው የህክምና ግብአቶች ደህንነታቸው ጠብቀው ለተጠቃሚው እንዲደርሱ በቂ ማቀዝቀዣ ማስፈለጉ ይታመናል። በተለይም እንደ ክትባት ኢንሱሊን፣ የላብራቶሪ ሪኤጀንቶች እና ሌሎች የህክምና ግብአቶችን ለማከማቸት የሚያገለግል የቅዝቃዜ ሰንሰለት የተገጠመላቸው መጋዝኖች ናቸው ዛሬ የተመረቁት። እስካሁን የነበረው የማቀዝቀዝ አቅም 300 ሜትር ኪዩብ ብቻ ስለነበረ መድሃኒቶችን በሚፈለገው ደረጃ ለማስቀመጥ ምቹ ቦታ አለመኖሩ ችግር ሆኖ መቆየቱን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሎኮ አብረሃም ተናግረዋል። አሁን የተመረቀው የማቀዝቀዝ ሰንሰለት በፊት ከነበረው በሶስት እጥፍ የሚተልቅ በመሆኑ የነበረውን ችግር የሚፈታ ነውም ብለዋል። በቀጣይም ሌላ የማቀዝቀዠ ሰንሰለት መጋዘኖች እየተሰሩ ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ሁለት ባለ 300 ኪዩቢክ ሜትር ማቀዝቀዣ እየተገነባ መሆኑ ተገልጿል። በአመቱ መጨረሻም ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል። ይህ ከሆነ በኋላ መድሃኒቶችን የደህንነት ደረጃቸው ምንም አይነት ስጋት ሳይኖር ለማጠራቀምና አቅርቦትን ለማቀላጠፍ ይረዳል ብለዋል። የተገነባው ማቀዝቃዣ ዘመናዊ በመሆኑ ካሁን በፊት ያጋጥም የነበረውን ችግር የሚፈታ መሆኑም ጭምር ተገልጿል። ይኸ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስወጣ ማቀዝቀዣ በዩኒሴፍ እርዳታ የተገኙ ማቀዝቀዣዎችን ተጠቅመው በተቋሙ ባለሙያዎች መገንባቱም ተገልጿል። በመጨረሻም በእውቀትም ሆነ በገንዘብ ድጋፍ ላበረከቱ አጋር አካላት የዕውቅና ሽልማት ተሰጥቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም