መድኃኒት ቤቶች በምሽት ዝግ ስለሚሆኑ መቸገራቸው በጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

78

ኢዜአ ታህሳስ 24 / 2012 መድኃኒት ቤቶች ከቀን ውጭ የምሽት አገልግሎት ስለማይሰጡ ለድንገተኛ ህመም ባለሙያ ያዘዘላቸውን መድኃኒት የሚገዙበት በማጣት መቸገራቸውን በጎንደር ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ጤና መምሪያ በበኩሉ የግል  መደኃኒት ቤቶች  አገልግሎቱን እንዲጀምሩ የሚሰራ መሆኑን ገልጿል።

የመንግስት የጤና ተቋማት መድኃኒት የማቅርብ ግዴታ እንዳለባቸውም  ያመለከተው ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ነው።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ተመስገን ንብረት እንዳሉተ ቀደም ሲል በከተማዋ የሚገኙ መድኃኒት ቤቶችና መደብሮች የ24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጡ ነበር።

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ግን ሁሉም መድኃኒት ቤቶች ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ አገልግሎት መስጠት በማቋረጣቸው በሌሊት ለሚያጋጥም ድንገተኛ ህክምና መድኃኒት ለመግዛት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

"ባለፈው ወር ህፃን ልጀ ታሞ ከሌሊቱ አምስት  ሰዓት ከግል ጤና ጣቢያ ወስደው ቢያሳክሙም የታዘዘለትን መድኃኒት በጊዜው ማግኘት ባለመቻሌ በህመም ሲሰቃይ አድሯል ብለዋል።

የሚመለከተው የመንግስት አካል ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በአስቸኳይ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ወይዘሮ ጠረፍወርቅ አስማረ በበኩላቸው በመንግስት ጤና ተቋማት የሚፈለጉ ሁሉም መድኃኒቶች ተሟልተው ስለማይገኙና የግሎቹ  ደግሞ በምሽተ ዝግ ስለሚሆኑ መድኃኒት ገዝተው መጠቀም እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

በከተማዋ የመድኃኒት ቤት ባለቤት  አቶ በላይ ከበደ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል መድኃኒት ቤቶች ወረፋ ወጥቶላቸው አዳር ይሰሩ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ መቋረጡን ገልጸዋል።

በምሽት ይሰጡት የነበረውን አገልግሎት በገበያ ማጣት ምክንያት መቋረጣቸውን ጠቅሰው፤ አገልግሎቱ እንዲጀመር የሚመለከተው አካል የሚደርገው እገዛ እንደሌለም ጠቁመዋል።

 የ24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት የተቋረጠው ከገበያ ማጣት ባለፈ የአካባቢው ሰላም አስተማማኝነት ስለሌለው የተፈጠረ ችግር መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የመድኃኒት ቤት ባለቤት ወይዘሮ ወርቄ ላቀው ናቸው።

የከተማዋ አስተዳደር ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አደም  እንዳሉት ቀደም ሲል የ24 ሰዓት  አገልግሎት በከተማዋ ይሰጥ ነበር፤ ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጧል።

በዚህም ህብረተሰቡ መቸገሩን ገልጸው "አሁን ላይ የተረጋጋ ሰላም በመፈጠሩ ባለንብረቶቹ በማነጋገር መምሪያንና አሰራርን መሰረት በማድረግ አገልግሎቱን እንዲጀምሩ  ይደረጋል "ብለዋል።

በከተማዋ 65 የግል መድኃኒት መደበር እንዲሁም አንድ የቀይ መስቀል ማህበር መድኃኒት ቤት እንደሚገኙ አመልክተዋል።

በክልሉ ጤና ቢሮ ጤናና ጤና ነክ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መንበሩ ፍጹም በበኩላቸው በታላላቅ ከተሞች 24 ሰዓት የሚያገለግሉ የመንግስት ጤና ተቋማት እንዳሉ ተናግረዋል።

የመንግስት ጤና ተቋማት ማንኛውንም ለድንገተኛ የሚሆን መድኃኒት የመያዝ ግዴታ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ መድኃኒቱ ከማለቁ በፊትም ማመልከትና መተካት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።

በመድኃኒት አቅርቦትና ስርጭት እጥረት በወቅቱ የመተካት ችግር ካልኖረ በቀር የመንግስት የጤና ተቋማት መድኃኒት የማቅርብ ግዴታ እንዳለባቸውም አስረድተዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት የግል መድሃኒት ቤቶች ደግሞ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚገደዱት መመሪያና አሰራርን መሰረት በማደረግ በቀን ለስምንት  ሰዓት  ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም