ጥቅም ላይ ሳይውሉ ለቀሩ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ መስህቦች ትኩረት ሊሰጥ ይገባል--- የመቀሌ ነዋሪዎች

93
መኢዜአ ታህሳስ 24 / 2012  በመቀሌ ከተማና አካባቢው ለቱሪስት መስህብ አገልግሎት ሳይውሉ ለቀሩ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥፈራዎችና ቅርሶች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ነዋሪዎች ገለጹ። ስፍራዎቹና ቅርሶቹን በማልማትና በማስተዋወቅ ለቱሪዝም መስህብነት ማዋል እንደሚገባም ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል። የከተማው ነዋሪና የታሪክ መምህር አቶ አድማሱ ተመስገን በከተማውና አካባቢው በጣሊያን ወራራ ወቅት ጦርነት የተካሄደባቸው ቦታዎችና የሰማዕታት መቃብር ስፍራዎች ለቱሪዝም አገልግሎት መዋል ሲገባቸው ያለጥቅም ተቀምጠዋል። ጥንታዊ አብያተክርስቲያናት፣ ገዳማት፣ መስጊዶችና የነገስታት መኖሪያ ሕንጻዎችም ለዘርፉ ጥቅም እንዲውሉ አለመደረጉን ጠቅሰዋል። "በከተማው የአጼ ዮሐንስ ቤተ-መንግስት፣ የእንደኢየሱስ ተራራ ጥንታዊ ቤተክርስቲያን፣ የጣሊያን መቃብር እና መሰል ታሪካዊና ሃይማኖታዊ መስህቦች ለቱሪዝም ዘርፍ ጠቀሜታ እየሰጡ አይደለም" ያሉት ደግሞ አቶ ሙሉጌታ ተረፈ ናቸው። በቤተ- መንግሰቱ እና በቤተ- ክርሰትያኑ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቅርሶችም በእንክብካቤ እጦት ለብልሽት መጋለጣቸውን ጠቁመዋል። ነዋሪዎቹ መስህቦቹን በማልማትና በማስተዋወቅ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም አመላክተዋል። የመቀሌ ከተማ የባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መረሳ ሕሉፍ በከተማው የሚገኙ የቱሪዝም እምቅ ሃብቶችን የማስተዋወቅ ሥራ ባለመሰራቱ  አብዛኞቹ በቱሪስቶች እየተጎበኙ እንዳልሆነ ተናግረዋል። "በመቀሌ ኩሓ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ጥንታዊ የጨርቆስ ቤተክርስቲያን፣ የአርኪዎሎጂ ቁፋሮ የሚያስፈልጋቸው ስፍራዎች፣ የጨለዓንቋና እንዳማርያም ደሓን ፋፏቴዎችም ለቱሪስት መስህብነት ሊውሉ ከሚችሉ ስፍራዎች የሚጠቀሱ ናቸው" ብለዋል። ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ታሪካዊና ጥንታዊ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎቹ ጥቅም ላይ ለማዋል ካርታ እየተዘጋጀላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል ። በጣሊያን ወራራ በአውሮፕላን ድብደባ ጉዳት ደርሶበት የነበረውን የቀዳማይ ወያነ የገበያ ማዕከል፣  ባህላዊ የህድሞ ቤቶችና ሌሎች ጥንታዊ ቅርሶች ያሉበት ሁኔታ የሚያሳይ ዝርዝር ጥናት መጠናቀንቁም አቶ መረሳ ጨምሮረው ገልጸዋል። ባህላዊ የህድሞ ቤቶችና ሌሎች ጥንታዊ ቅርሶች ያሉበት ሁኔታ የሚያሳይ ዝርዝር ጥናት መጠናቀቁም አቶ መረሳ ጨምሮረው ገልጸዋል። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ  የጥንት ስነ ምህዳርና ቅርስ ጥበቃ ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሃፍቶም ተክሉ በበኩላቸው በከተማው የሚገኙ ቅርሶችን ለማስተዋወቅ ከአስተዳደሩ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የቱሪስት መረጃ ማዕክል የመክፈት፣ ካርታና መመሪያ የማዘጋጀት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ነው የጠቀሱት። እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ በአሁኑ ወቅትም ለአስጎኚኝዎችም ስልጠና እየተሰጠ ነው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም