የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ኃይል አዛዥ ጀነራል ቃሲም ሶሌኢማኒ በአሜሪካ ወታደሮች ተገደሉ

ኢዜአ፤ ታህሳስ 24/2014 የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ  ኃይል አዛዥ ጀነራል ቃሲም ሶሌኢማኒ ኢራቅ ውስጥ በአሜሪካ ወታደሮች ተገድለዋል፡፡ ጀነራል ቃሲም የተገደሉት በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ ኤር ፖርት አቅራቢያ በመኪና ሲንቀሳቀሱ በነበሩበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡ ጀነራል ቃሲም ሶሌኢማኒ በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ እንደነበሩ ይነገራል። የአሜሪካ የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት ፔንታጎን ጀነራል “ሶሌኢማኒ የተገደሉት በፕሬዝደን ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ ነው” ብሏል። የኢራን ዋና መሪ አያቶላህ አሊ ከሃመኒ ጥቃቱን በተመለከተ  በሰጡት መግለጫ “ወንጀለኞቹ ከባድ የበቀል እርምጃ ይጠብቃቸዋል” ብለዋል ፡፡ ለሶስት ቀናትም ብሄራዊ የሀዘን ቀን እንደሚታወጅም አስታውቋል፡፡ የጀነራሉ መገደል በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ያለውን ውጥረት እንዳያባብስ ስጋት ፈጥሯል፡፡ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ ላይ እስካሁን  ምንም አስተያየት አልሰጡም ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም