የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በመስቀል አደባባይ የደረሰውን ፍንዳታ አወገዘ

73
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የደረሰውን ፍንዳታ በጽኑ እንደሚያወገዝ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ላመጧቸው ለውጦች ድጋፍና እውቅና መስጠትን ዓላማ ያደረገ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄዷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰልፉ ላይ በመገኘት ለታዳሚዎች መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ፍንዳታ መድረሱ ይታወቃል። የደረሰውን ፍንዳታ በጥብቅ እንደሚያወግዝ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ላይ በደረሰዉ ጉዳት በአደጋው ለተጎዱ ቤተሰቦች እና አካላት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘንም ገልጿል። ለመላ ኢትዮጵያዊያንም መጽናናትን ተመኝቷል። አጥፊዎችን ወደ ህግ ለማቅረብ መንግስት እና የፀጥታ ሃይሎች ለሚያደርጉት ጥረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፏል ምክር ቤቱ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ መስቀል አደበባይ በተካሄደው ሰልፍ በደረሰው ፍንዳታ ጉዳት በደረሰባቸው ዜጎች የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን ገልጻለች። ክስተቱ አስደንጋጭ ቢሆንም የህዝቡን የአንድነት፣ የፍቅር፣ የመተሳስብና የይቅር ባይነት ጉዞ እንደማይገታው ቤተክርስቲያኒቷ እንደምታምን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ተናግረዋል። ለዚህም መላው ኢትዮጵያውያን ጥላቻና ዘረኝነትን አስወግደው የጀመሩትን የተስፋ፣ የሰላምና የአንድነት ጉዞ በጋራ ሆነው በተፈጠረው ነገር ሳይረበሹ በፍጹም ጽናት እንዲያስቀጥሉ አሳስበዋል። ለተጎዱ ዜጎችና የተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን የተመኙ ሲሆን በየሆስፒታሉ ህክምና እያገኙ ያሉ ዜጎች በፍጥነት እንዲያገግሙ ምኞታቸውን ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም